`ሪልስ` የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ ከቲክቶክ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ ታውቋል
ፌስቡክ አጫጭር ቪዲዮችን ማጋራት የሚያስችል `ሪልስ` የተባለ አዲስ አገልግሎት ይዞ ብቅ ማለቱን በትናትናው እለት አስታውቋል።
አዲሱ `ሪልስ` የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በ150 ሀገራት ላይ መለቀቁንም ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ አስታውቋል።
ሜታ ኩባንያ `ሪልስ` የተባለውን የቪዲዮ አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ በኢንስታግራም ላየ በአውሮፓውያኑ በ2020 እንዲሁም በፌስቡክ ላይ ደግሞ በ2021 ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።
ፌስቡክ ይህንን የቪዲዮ አገልግሎት ይዞ ብቅ ያለው በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ የመጣውን የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ ቲክቶክን ለመገዳደር እንደሆነም ታውቋል።
የሜታ መስራች እና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ፤ አዲሱ የሪል የቪዲዮ ማጋሪያ አገልግሎት ከትናንት ምሽት ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በፌስቡክ ላይ መለቀቁን አስታውቋል።
አዲሱ የሪል አገልግሎት ተጠቃሚዎች በገጻቸው ላይ እየቀረጹ በሚጭኗቸው ቪዲዮዎች ገንዘብ ማግኘት እንደሚችሉም ነው የተነገረው።
በተጨማሪም በቪዲዮዎቹ መካከል ማስታወቂያዎች በማስገባት የቪዲዮዎቹ ባለቤቶች ገቢ ማግኘት የሚችሉበት አስራር እንዳለውም ታወቋል።
ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የሆነው ፌስቡክ በፈረንጆቹ 2022 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ አስደንጋጭ የሆነ የተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስ እንዳጋጠመው ተነግሯል።
ፌስቡክ ከተቀናቃኞቹ ቲክቶክ እና ዩትዩብ የገጠመው ፉክክርም ለተጠቃሚዎቹ መቀነስ በምክንያትነት መቀመጡ ይታወሳል።