ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በእጅጉ መቀነሱ ተነገረ
ለፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስም ምክንያትም ከደህንነትና መረጃ አሳልፎ ከመስጠት ጋር ተያየዞ የሚቀርቡበት ክሶች ናቸው
በዓለም አቀፍ ደረጃ እለታዊ የፌስቡክ ተጠሚዎች ቁጥርም ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል
ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የሆነው ፌስቡክ ለመጀመሪያ ጊዜ አስደንጋጭ የሆነ የተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስ እንዳጋጠመው ተነግሯል።
ሜታ የተባለውና ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ኩባንያ ባወጣው ሪፖርት በመጀመሪያው የፈረጆቹ 2022 ሩብ ዓመት የተጠቃሚዎቹ ቁጥር መቀነሱን አስታውቋል።
ፌስቡክን ጨምሮ ሌሎችን የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በስሩ የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ የስቶክ ገበያም በ20 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ኩባንያው ባወጣው ሪፖርቱ ገልጿል።
የስቶክ ገበያው መቀነስም ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ በስቶክ ገበያው ላይ 200 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የገበያ ዋጋን እንዲያጣ እንዳደረገውም ተነግሯል።
ከዚህ ውጪም በዓለም አቀፍ ደረጃ እለታዊ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱንም ኩባንያው አሳውቋል።
በዚህም መሰረት ባለፈው ሩብ ዓመት የነበረው 1.930 ቢሊየን እለታዊ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በዚህኛው ሩብ ዓመት ወደ 1.929 ቢሊየን መውረዱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ለፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስ በዋነኝነት ከተቀመጡት ውስጥ የተጠቃሚዎችን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር እንዲሁም የተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፎ ከመስጠት ጋር የሚነሱበት ክሶች ዋነኛው ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ፌስቡክ ከተቀናቃኞቹ ቲክቶክ እና ዩትዩብ የገጠመው ፉክክርም ለተጠቃሚዎቹ መቀነስ በምክንያትነት ተቀምጧል።