ሰሜን ኮሪያ ወደ ጃፓን ባለስቲክ ሚሳኤል አስወነጨፈች
ሚሳኤሉ በ50 ኪሎሜትር ከፍታ ከ250 ኪሎሜትር በላይ መጓዙን ነው የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ባለፈው ሳምንት ወደ ባህር ክልሌ የተወነጨፈብኝ ሚሳኤል ሶቪየት ሰራሽ መሆኑን ደርሼበታለው ብላለች
ሰሜን ኮሪያ ወደ ጃፓን ባለስቲክ ሚሳኤል አስወነጨፈች።
የጃፓን የባህር ዘብ የባለስቲክ ሚሳኤሉ መወንጨፉ ሪፖርት በተደረገ በደቂቃዎች ልዩነት ወደ ባህር መግባቱን ገልጿል።
ሚሳኤሉ በ50 ኪሎሜትር ከፍታ ከ250 ኪሎሜትር በላይ መጓዙን ያሳወቀው ደግሞ የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር ነው።
ሚኒስትሩ ያሱካዙ ሃማዳ ፥ "የፒዬንግያንግን ድርጊት እናወግዛለን፤ ከቤጂንግ ጋር በመነጋገር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመፈለግ እየሞከርን ነው" ብለዋል።
ደቡብ ኮሪያም አይነቱ ገና በመጣራት ላይ የሚገኝ የባለስቲክ ሚሳኤል ከወደ ሰሜን ኮሪያ መወንጨፉን ገልፃለች።
ሴኡል ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ባህር ዳርቻዋ አቅራቢያ የተወነጨፈው ሚሳኤል "ኤስ ኤ - 5" የተሰኘ የሶቪየት ዘመን አጭር ርቀት ሚሳኤል መሆኑን ደርሼበታለው ብላለች።
ይህም ሰሜን ኮሪያ ከሰሞኑ ያደረኩት ሙከራ የይስሙላ ወይም ሲሙሌሽን ነው ማለቷ ይታወሳል።
የሚሳኤል ሙከራው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ ላይ የሚገኙትን አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ለማስጠንቀቅ ያደረኩት ነው ማለቷንም ሬውተርስ አስታውሷል።
በወደቀው ስብርባሪ ላይ የተደረገው ምርመራ ግን ሶስት ሜትር ርዝመት እና ሁለት ሜትር ስፋት ያለው ኤስ ኤ - 5 ሚሳኤል እንደ አውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ የተሰራ አውሮፕላን መቃወሚያ ነው ብሏል የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር።
ይሄን ሚሳኤል ሩስያ በዩክሬኑ ጦርነትጥቅም ላይ እንዳዋለችው በመግለፅም ፒዬንግያንግ ከፀብ አጫሪ ድርጊቷ እንድትቆጠብ አሳስቧል።
ኤስ ኤ- 5 ሚሳይል
ሶቪየት ሰራሹ አየር መቃወሚያ አሁንም ድረስ በበርካታ ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ይነገራል።
ሚሳኤሉ በተለይ ቦምብ ጣይ ጄቶችን እና ከፍታ ላይ የሚገኙ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ይውላል።
ሰሜን ኮሪያም ይህንኑ የሰማይ ላይ በራሪዎችን ወደ ምድር የሚቀላቅል መሳሪያ በፈረንጆቹ በ1980ዎቹ በእጇ ማስገባቷን ነው መሰጃዎች የሚያሳዩት።
ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር በሚሳኤል ሙከራ እየተነታረከች ያለችው ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ለዚህ ወቀሳ ምላሽ አልሰጠችም።
ፒዬንግያንግ ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ የመጀመሪያውን የኒዩክሌር ሙከራ ልታደርግ ተዘጋጅታለች የሚሉት አሜሪካ እና የቀጠናው ወዳጆቿ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ዛቻም በጉልህ እየተደመጠ ነው።