ፌስቡክን ጨምሮ የሜታ መተግበሪያዎች ላይ ያጋጠመው ምንድን ነው?
ከደቂቃዎች በፊት ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ሜሴንጀርን ጨምሮ የሜታ መተግበሪያዎች መስራት አቁመዋል
ተጠቃሚዎች በመጠቀም ላይ እያሉ ድንገት ከሚጠቀሙበት መተገበሪያ እንደወጡ ተናግረዋል
ፌስቡክና ኢንስታግራምን ጨምሮ የሜታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች አሁን ላይ መስራት ማቆማቸው ሪፖርቶች በመውጣት ላይ ይገኛሉ።
በርካቶች በመጠቀም ላይ እያሉ ድንገት ከማህበራዊ ትስስር ገጻው መውጣታቸውን (log Out) እየተደረጉ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ ችግሩ ኢትዮጵያና አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ የዓለም ክፍል አጋጥሟል።
ተመልሶ ለመግት በሚሞክሩበት ጊዜም ትክክለኛውን ይለፍ ቃል (ፓስወርድ) እያስገቡም የተሳሳተ ፓስዎርድ ነው እያለ እንደሚመልስ እና ለመቀየር ሲሞክሩም አልሰራ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ዳዎን ዲቴክተር የተባለ ድረ ገጽም በመላው ዓለም ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ፌስቡክ አልሰራ አለ የሚሉ ሪፖርቶችን መቀበሉን አስታውቋል።
ትሪድስ የተሰኘው የትዊተር ተፎካካሪ የሜታ መተግበሪያም አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።
የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ ኩባንያ በጉዳዩ ላይ በሰጠው ማብራሪያ፤ “ኢንጂነሮቻችን ችግሩን በአፋጠኝ ለመቅረፍ እየሰሩ ነው” ብሏል።
የሜታ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኤንዲ ስቶን፤ በቀድሞ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጽ ላይ፤ ኩባንያው በዓለም ዙሪያ ችግሩ እንዳጋጠመ መረዳቱን አስታውቀዋል።
ሜታ ኩባንያ በአሁኑ ጊዜ ቸግሩን ለመቅረፍ እየሰራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ያለምንም ችግር እየሰራ ያለው የሜታ መተግበሪያ ዋትስአፕ ብቻ መሆኑን ዳውንዲቴክተር አስታውቋል።
ሜታ በ2021 ተመሳሳይ ችግር የገጠመው ሲሆን፥ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ለስአታት አልሰራ ማለታቸው ይታወሳል።