የፌስቡክ አካውንታችን ከእጃችን ቢወጣ መመለሻው መንገድ ምንድን ነው?
ደካም የይለፍ ቃል መጠቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ልብ የማንላቸው ጉዳዮች የፌስቡክ አካውንታችን ከቁጥጥራችን ውጭ ያደርጉታል
በዚህ ጽሁፍም የፌስቡክ አድራሻችን ቢጠለፍ እንኳን በፍጥነት የምናስመልስበትን መንገድ እንጠቁማኋለን
ብዙዎቻችን ዘወትር ለምንጠቀመው ፌስቡክ ደካም (ቁጥር፣ ምልክቶች እና ፊደላትን ያላካተተ) የይለፍ ቃል የመጠቀም ክፉ ልማድ አለን።
ረዘም ያለና ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም ከጀመርንም በድጋሚ ስንጠቀም እንዳይጠይቀን የማስታወስ ስራውን ለፌስቡክ እንተውለታለን።
ችግሩ ስልካችን ወይም ላፕቶፓችን ሲጠፋ ወይም በቅርብ ስናጣው እንዲሁም በቢሮ ወይም በሌላ ሰው ስልክ ከፍተን አካውንታችን በሌላ ሰው እጅ ሲወድቅ መስተዋል ይጀምራል።
ዘወትር የምንጠቀምበት ስልክ ቢጠፋ አልያም የይለፍ ቃላችን ብንረሳው ወዲያውኑ አካውንታችን መመለሻ መንገድ እንዳለ ብናውቅም ስንቶቻችን ጠንካራ የደህንነት ማረጋገጫዎችን ገቢራዊ አድርገናል የሚለው አጠያያቂ ነው።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት 5 መንገዶችም የፌስቡክ አካውንታችን በጠላፊዎች በቀላሉ እንዳይሰበር ያግዛሉ፤ ሚስጢር ገመናችን የያዘው አካውንታችን በሌላ ሰው እጅ ቢገባ እንኳን በፍጥነት ማስመለስ ያስችሉናል።
1. የሴኩሪቲ ሴቲንግ ፍተሻ
በቅድሚያ የፌስቡክ አካውንታችን ደህንነት ለማረጋገጥ ቀጣዩን ፍተሻ ያድርጉ፦
Account - Settings & privacy - Settings - Security and Login screen - Check Your Important Security Settings
ይህን ሂደት ስናጠናቅቅ ሶስት ነገሮችን ይነግረናል፤ የሚጠቀሙት የይለፍ ቃላት ጠንካራ ነው ወይስ ደካማ? ፣ የማንቂያ ደወል እንዲደርስዎ ፈቅደዋል (login alerts) ወይ? እንዲሁም በስልክ እና በኢሜል እርሶ እየከፈቱ መሆኑን ማረጋገጫ እንዲሰጡ (two-factor authentication) ፈቅደዋል? የሚሉትን ይመልሳል።
ይህ ቀዳሚውና መሰረታዊው የፌስቡክ አካውንታችን ደህንነት ማረጋገጫ መንገድ ነው፤ ወደኋላ እንዴት ያግዘናል የሚለውን እንመለስበታለን።
2. የተለያዩ አድራሻዎቻችን ማካተት እና በየጊዜው ማስተካከል
የፌስቡክ የይለፍ ቃል ወይም ፓስወርድ ብንዘነጋ በፍጥነት በአዲስ ተክቶ ለመጠቀም የኢሜል እና ስልክ ቁጥራችን ማካተት ቀላሉ ዘዴ ነው፤ በስልክ ወይም በኢሜል ብቻ መክፈት ስልካችን ቢጠፋ (ሲም ካርዱን ድጋሚ ማውጣት የማንችልበት ሁኔታ ቢፈጠር) አልያም የኢሜላችን ፓስወርድ ቢንዘነጋው ፌስቡካችን ከእጃችን ወጥቶ እንዲቀር ያደርጋል።
በመሆኑም እየተጠቀምንባቸው የሚገኙ የኢሜል እና ስልክ ቁጥሮችን ከአንድም ሁለት ብናስገባ የተሻለ ነው።
የስልክ ቁጥሮችንም ሆነ የኢሜል አድራሻዎች ለውጥ ካለም በፍጥነት መቀየር ወይም አፕዴት ማድረግ ይገባል።
ተጨማሪ የኢሜል አድራሻ እና ስልክ ቁጥር ለማስገባት
Account - Settings & privacy - General account settings - Contact - Edit /
Settings – Account - personal and account information – phone number/email- edit
ቢያንስ ሁለት ሁለት የኢሜል አድራሻና ስልክ ቁጥር ማስገባት ይመከራል። ፌስቡክ አዲሱን የኢሜል አድራሻ ወይም ስልክ ቁጥር እንዳስገባን ወደ የማረጋገጫ መልዕክት የሚልክ ሲሆን፥ ካረጋገጥንለት በኋላ የትኛውም ለውጥ ሲኖር ወዲያውኑ ባስመዘገብናቸው የኢሜልና ስልክ ቁጥር አድራሻዎች ያሳውቀናል። ይህም ከእውቅናችን ውጭ የሚደረግ ነገር ካለ ማቋረጥ ያስችለናል።
3. የይለፍ ቃል መለወጥ
ተመሳሳይ የይለፍ ቃልን ጠንካራም ቢሆን ከአንድ በላይ ለሆነ የኦንላይን አካውንት መጠቀም አይመከርም፤ አደገኛም ነው። የይለፍ ቃላት በተለያየ ምክንያት በጠላፊዎች እጅ የመግባት እድል ስላላቸውም ቢያንስ በአንድ አመት ውስጥ ሊለወጥ ይገባዋል።
Settings - Security and Login settings - Change password – edit /
Settings – Account – password and security - Change password
4. የማንቂያ ደወል እንዲደርስዎ ይፍቀዱ
የፌስቡክ አካውንትዎ ከአዲስ አድራሻ ለመክፈት ሙከራ ሲደረግ ማንቂያ መልዕክት (Login alert) እንዲልክ መፍቀድ ሌላኛው የፌስቡክ አካውንታችን ደህንነት ማረጋገጫ ነው።
የማንቂያ መልዕክቱ በፌስቡክ፣ በሜሴንጀር እና በኢሜል አድራሻዎ እንዲደርስዎ ማድረግ ይችላሉ።
5. ሁለት ሂደት የሚከተል ስርአት (two-factor authentication)
ከላይ ከተዘረዘሩት የፌስቡክ ደህንነት ማረጋገጫ መንገዶች ሁሉ ይሄኛው እጅግ ወሳኙ ጋሻ ነው።
እንኳን ሌላ ሰው ራሳችንም ከአዲስ ሞባይልም ሆነ ላፕቶፕ ፌስቡካችን ስንከፍት ተጠራጥሮ ይሁንታ እንድንሰጠው መልዕክት ይልካል፤ በስልክ ቁጥር እና በኢሜላችን የሚላከው የደህንነት ቁጥርን ካላስገባን በስተቀር ፌስቡካችን መክፈት አንችልም። ይህም የይለፍ ቃላችን በሌላ ሰው ቢታወቅ እንኳን ከተለመደው ስልክና ላፕቶፕ ውጭ እንዳይከፈት በማድረግ ሙሉ በሙሉ አካውንታችን እንዳይጠለፍ ያደርጋል።
ቀጥሎ ያለውን ሂደት ተከትለው የtwo-factor authentication ፈቃድ ይስጡ፦
Settings - Security and Login- Two-factor authentication - Edit /
Settings – Account – password and security - Two-factor authentication
የtwo-factor authentication በሶስት አማራጮች ነው የደህንነት ማረጋገጫ መልዕክቶችን የሚልከው፤ በስልካችን በጽሁፍ መልዕክት፣ እንደ Google Authenticator እና Duo ባሉ ሶስተኛ ወገን መተግበሪያዎች አማካኝነት እና ቀድሞ በሚላኩ ሚስጢራዊ ቁጥሮች ወይም ሴኩሪቲ ኮድስ።
ከላይ ከጠቀስናቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ባለፈ ፌስቡክ ከተጠቀምን በኋላ ዘግቶ መውጣትን (በተለይ በቢሮ እና በሌሎች ሰዎች ስልክና ላፕቶፕ ስንጠቀም) ልማድ ልናደርገውና የይለፍ ቃላት ማስታወስና መለዋወጥን ባህል ልናደርገው ይገባል።
በየእለቱ ከ2 ቢሊየን በላይ ሰዎች የሚጠቀሙት ፌስቡክ ደህንነቱ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ በየግዜው የሚያደርጋቸውን ማሻሻያዎችንም መከታተሉ አይከፋም።