ሩሲያ ፌስቡክን እና ኢንስታግራምን በአሸባሪነት ፈረጀች
ሁለቱን የአሜሪካ ተቋሜት በጽንፈኝነት የተፈረጁት ጸረ ሩሲያ ይዘቶችን በማሰራጨቱ ነው
ሜታ ኩባንያ በበኩሉ “ሞት ለሩሲያ” የሚሉ ይዘቶችን እንደሚያበረታታ አስታውቋል
ሩሲያ ፌስቡክን እና ኢንስታግራምን በአሸባሪነት ፈረጀች።
የአሜሪካ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆኑት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በሩሲያ በሽብርተኝነት እና ጽንፈኝነት ተፈርጀዋል።
ሩሲያ የሜታ ኩባንያ ንብረት የሆኑት ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን በአሸባሪነት የፈረጀችው ጸረ ሩሲያ ይዘቶች እንዲሰራጩ በማድረጉ እንደሆነ አስታውቃለች።
ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ካለፈው መጋቢት ጀምሮ በሩሲያ እንዳይሰራጩ የታገዱ ቢሆንም ሩሲያዊያን ግን በቪፒኤን በመታገዝ ሁለቱንም የማህበራዊ ትስስር ገጾችን እንደሚጠቀሙ ተገልጿል።
ሜታ ኩባንያ በበኩሉ በሩሲያ የቀረበበትን ክስ ያልካደ ሲሆን "ሞት ለሩሲያ" የሚሉ ይዘቶች በነዚህ ትስስር ገጾች እንዲሰራጩ መፍቀዱን አስታውቋል።
ይሁንና "ሞት ለሩሲያ" የሚሉት ይዘቶች ንጹሀንን ሳይሆን በዩክሬን ምድር የገቡ የሩሲያ ወታደሮችን የሚመለከት ነው ብሏል።
የሩሲያ አዲስ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ሽብርተኝነት ፍረጃ በሜታ ኩባንያ ስር ያለው ዋትስ አፕ የተሰኘው ድርጅት እገዳው እንደማይመለከተው አርቲ ዘግቧል።
ሜታ ኩባንያ በሩሲያ የተላለፈበትን የሽብርተኝነት ውሳኔ በሞስኮ ባለ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንዳስገባም ተገልጿል::በሩሲያ ከፌስቡክ ይልቅ ኢንስታግራም የበለጠ ብዙ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ዘገባው ላይ ተጠቅሷል።