ኬንያ ፌስቡክን ልትዘጋ እንደምትችል አስጠነቀቀች
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሚካሄድ ይጠበቃል
ኬንያ ፌስቡክ ከጥላቻ ንግግር ጋር በተያያዘ አሰራሩን እንዲያስተካክል አሳስባለች
ከአንድ ሳምንት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምታካሂደው ጎረቤት ሀገር ኬንያ ፌስቡክን አስጠንቅቃለች።
ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጩ እንዲያደርግ በኬንያ መንግስት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።
የኬንያ የውህደት እና ትብብር ሚንስትር እንዳሳወቀው ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ በፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች እየጨመሩ መጥተዋል ብሏል።
በመሆኑም እነዚህ የጥላቻ ንግግሮች እየጨመሩ የመጡት ፌስቡክ እርምጃ ባለመውሰዱ ነው የምትለው ኬንያ ኩባንያው አሰራሩን እንዲያስተካክል አስታውቃለች።
ፌስቡክ እነዚህን የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጩ ካላደረገ ፌስቡክ በኬንያ ምድር እንዳይሰራ እግድ ሊተላለፍበት እንደሚችል ኬንያ አስጠንቅቃለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጩ እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን የገለጸው የኬንያ መንግስታዊ ተቋም ስርጭቶችን ለመከላከል ግሎባል ዊትነስ ኤንድ ፎክስግሎቭ ከተሰኛ ሌላ ተቋም ጋር እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።
ፌስቡክ በኬንያ መንግስት የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተቀብሎ በሰባት ቀናት ውስጥ ማስተካከያ ካላደረገ በኬንያ ደህንነት ላይ ችግር ስለሚፈጥር እርምጃ እንወስዳለንም ብሏል ይሄው መንግስታው ተቋም።
ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮችን ይቆጣጠራል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አጥኚዎች በፈረንጆቹ 2007 ላይ በተካሄደው ምርጫ ወቅት ተሰራጭተው የነበሩ የጥላቻ ንግግሮችን በእንግሊዝኛ እና ስዋሂሊ ቋንቋዎች ፌስቡክ ላይ እንዲለቀቁ ያደረጉ ቢሆንም በፌስቡክ ኩባንያ ሳይታገዱ ቀርተዋል ተብሏል።
ፌስቡክ ኩባንያ በበኩሉ በሐምሌ ወር ብቻ ከ37 ሺህ በላይ የጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩ ገጾችን እና 42 ሺህ የድርጅቱን ስነ ምግባር የጣሱ ገጾችን ዘግቻለሁ ብሏል።