ሪክ ማቻር በሚመሩት ኤስፒኤልኤም አይ ኦ ፓርቲ ውስጥ ያሉ አካላት በሁለት ተከፍለው መታኮሳቸው ተገልጿል
በደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በሚመራው ኤስፒኤልኤም አይ ኦ ፓርቲ ውስጥ ክፍፍል መፈጠሩን ተገለጸ፡፡
በፓርቲው ውስጥ ተፈጥሯል በተባለው ክፍፍልም በሪክ ማቻር የሚመራ እና በጀነራል ሲሞን የሚመሩ ወታደሮች እንዳሉ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም በጀነራል ሲሞን የሚመሩት ወታደሮች በሪክ ማቻር በሚመሩ ወታደሮች ላይ ተኩስ መከፈታቸው ተገልጿል፡፡
ተኩሱ የተከፈተውም ሪክ ማቻርን ከኤስፒኤልኤም አይ ኦ ፓርቲ መሪነት ለማውረድ ሙከራ ከተደረገ ከሶስት ቀናት በኋላ ነው፡፡ በፓርቲው ውስጥ አፈንጋጭ እንደሆነ የተገለጸው እና በጀነራል ሲሞን የሚመራው ክንፍ ሪክ ማቻር የፓርቲው መሪ አለመሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ጀነራል ሲሞን፤ ከዚህ በኋላም ሪክ ማቻር ይመሩት የነበረው ኤስፒኤልኤም አይ ኦ ፓርቲ መሪ እኔ ነኝ ማለታቸውን የተገለጸ ሲሆን ለእርሳቸው ታማኝ የሆኑ ኃይሎችም በማቻር ወታደሮች ላይ ተኩስ ከፍተው እንደነበር ተገልጿል፡፡
ለሪክ ማቻር ታማኝ ሆኑት የፓርቲው ቃል አቀባይ ላም ፉል ጋብርኤል በጁባ ከተማ ለአል ዐይን ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ በጀነራል ሲሞን የሚመሩ ወታደሮች በካይዛን አካባቢ ተኩስ መክፈታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ተኩስም የሪክ ማቻር ወገን የሆኑ ወታደሮች ሁለት ጀነራሎችንና በርካታ ወታደሮችን መግደላቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ ውጊያው በገለልተኛ አካል እንዳልተጣራ የተገለጸ ሲሆን ከጀነራል ሲሞን ጋትዌች ዱዋል በኩል የተሰማ ነገር የለም ተብሏል፡፡
ጀነራል ሲሞን የኤስፒኤልኤም አይ ኦ መሪ እርሳቸው መሆናቸውን መግለጻቸው ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱ ተገልጿል፡፡ በሪክ ማቻር በሚመራው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል አዲስ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ጀነራል ሲሞን የፓርቲው መሪ መሆናቸውን የገለጹት ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በሚዋሰኑበት ሙጋይን አካባቢ ነው ተብሏል፡፡
ቃል አቀባዩ፤ በፓርቲው ወስጥ የማቻርን መሪነት ያልተቀበሉትና ተኩስ እንዲከፈት ያደረጉት ጀነራል ሲሞን እና ጀነራሎቻቸው ወደ ሱዳን ግዛት ማምለጣቸውን የሚያመለክቱ ታማኝ መረጃዎች ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሱዳን መንግስት እነዚህን ጀነራሎች እንዲያስራቸውም የማቻር ፓርቲ ቃል አቀባይ ጠይቀዋል፡፡