ዶናልድ ትራምፕ ለምርጫ ቅስቀሳቸው የቢትኮይን ልገሳዎችን መጠቀማቸው ይታወሳል
ስለ ቢትኮይን ሊያውቋቸው የሚገቡ ሰባት ዋና ዋና ነጥቦች ምን ምን ናቸው?
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከሶት ዓመት በፊት ስለ ቢትኮይን በሰጡት አስተያየት ቢትኮይን የማጭበርበሪያ ስልት ነው ብለው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ዋነኛ የቢትኮይን ደጋፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የቢትኮይን ደጋፊ መሆናቸውን በይፋ የተናገሩት ትራምፕ ለምርጫ ቅስቀሳቸው ሳይቀር የቢትኮይን ልገሳዎችን ተቀብለዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፍን ተከትሎ እንደ ቢትኮይን አይነት የምናባዊ መገበያያ ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ መገበያያዎች ዋጋቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በ87 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ሲሆን በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ወደ 100 ሺህ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
ቢቢሲ ዋጋው እያደገ ስላለው ቢትኮይን ልታውቋቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮች በሚል በሰራው ዘገባ እስከ አሁን ያሉ ክስተቶችን አስነብቧል፡፡
ጃፓናዊው ሶታሺ ናካሞቶ የቢትኮይን ፈጣሪ እንደሆኑ በስፋት ቢገለጽም ሶታሺ ማን እንደሆኑ የማይታወቁ ሲሆን በርካቶች የቢትኮይን ፈጣሪ እንደሆኑ ቢናገሩም ታማኝነትን ማግኘት አልቻሉም፡፡
በፈረንጆቹ 2008 ላይ እንደተፈጠረ የሚገለጸው ቢትኮይን አውስትራሊያዊው የኮምፒውተር ባለሙያው ክሬግ ራይት የቢትኮይን መስራች ሶታሺ ማለት እኔ ነኝ በሚል በፍርድ ቤት ለማስወሰን ቢጥርም ሶታሺ ነኝ የሚለውን ክርክር ማሸነፍ አልቻለም፡፡
በርካቶች ካናዳዊው የቢትኮይን ባለሙያ ፒተር ቶድ ትክክለኛው የቢትኮይን መስራች እሱ ነው ቢሉም ሶታሺ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡
ይሁንና እንግሊዛዊው ስቴፈን ሞላህ የቢትኮይን መስራቹ እሱ መሆኑን ተናግሮ ነገር ግን ይህንን ማንም አያምንም ሲል ከሰሞኑ ተናግሯል፡፡
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በ100 ሺህ ዶላር ሊመዘር እንደሚችል ተገለጸ
ግንቦት 2010 ላይ ላዝሎ ሀኒየች የተባለው የ19 ዓመት ተማሪ በቢትኮይን ግብይት የፈጸመ የመጀመሪያው ሰው ሲሆን በ41 ቢትኮይን ዋጋ አንድ ፒዛ ገዝቷል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ የቢትኮይን ዋጋ አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ እያለ አሁን እደረሰበት ደረጃ ለይ የደረሰ ሲሆን እንደ ኤልሳልቫዶር ያሉ ሀገራ በ2021 ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መገበያያ እንዲሆን ፈቃድ አግኝቷል፡፡
የሀገሪቱ መንግስትም 120 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ስድስት ሺህ ቢትኮይኖችን በመግዛት የሀገሬው ዜጋ ቢትኮይንን እንዲጠቀም እና ኩባንያዎችም ወደ ኤልሳልቫዶር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ካዛኪስታን የቢትኮይን አልሚዎች ወደ ሀገሯ እንዲመጡ ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ ሀገሪቱ ዋነኛ የዓለማችን የቢትኮይን አልሚ ኩባያዎች መሆን ችላለች፡፡
ይሁንና ኩባንያዎቹ ከፍተኛ ሀይል የሚጠቀሙ መሆናቸውን ተከትሎ ሀገሪቱ የሀይል እጥረት እንዲገጥማት ምክንያት ሆናችኋል በሚል ከፍተኛ ግብር ሲጣልባቸው ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡
የዌልስ ዜግነት ያለው ጀምስ ሆውልስ የተባለው ሰው 100 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ቢትኮይን ሀብት የነበረው ቢሆንም ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ይህ ሰው ገንዘቡን ተጭበርብሮ ቀርቷል፡፡
ይህን ተከትሎ በቢትኮይን ታሪክ ከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመበት ግለሰብ ሆኗልም ተብሏል፡፡
አሜሪካውው የኤፍቲኤክስ ምናባዊ ግብይት ኩባንያ መስራች የሆነው ሳም ባንክማን ፍራይድ የተባለው ሰው 32 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት እንዳለው ቢገለጽም አጭበርብሯል በሚል የ25 ዓመት እስር ተፈርዶበታል፡፡
የያዝነው 2024 ዓመት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በርካታ የዓለማችን ትላልቅ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች የቢትኮይን ግብይትን ከፈቀዱ በኋላ ቢትኮይን በታሪክ ከፍተኛውን ዋጋ አግኝቷል፡፡
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ከሰሞኑ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን የቢትኮይን ግብይት ማዕከል እድትሆን አደርጋለሁ ማለታቸው ይታወሳል፡፡