ቱርክ እና ሶሪያን በመታው ከባድ ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር ከ3700 በላይ ደረሰ
በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት ንዝረት ከቱርክ በተጨማሪ በአካባቢው ባሉ ሀገራት ጭምር ተሰምቷል
የቱርክ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ርዕደ መሬቱ “ታሪካዊ አደጋ” ነው ብለውታል
በቱርክ እና በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ግዛት የተከሰተውን ከባድ ርዕደ መሬት ተከትሎ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3 700 በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡
ርዕደ መሬቱ በቱርክ ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን አፓርታማዎችን አፈራርሶ ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት በተፈናቀሉ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሶሪያውያን ላይ የበለጠ ውድመት አስከትሏል።
በቱርክ ብቻ የሟቾች ቁጥር 2ሲሺህ 316 መድረሱን የሀገሪቱ የአደጋና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአደጋው 13 ሺህ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ጭምር ገልጿል፡፡
ይህም በ1939 (18ሺህ ሰዎች የሞቱበት) እንዲሁም 1999 (17 ሰዎች የሞቱበት) በኢስታንቡል አቅራቢያ የሚገኘውን ምስራቃዊ ማርማራ ባህር አካባቢ ካጋጠመው ተመሳሳይ መጠን ያለው ርዕደ መሬት በኋላ ያገጠመ የከፋ አደጋ ነው ተብሎለታል፡፡
በሶሪያም እንዲሁ እስካሁን ቢያንስ 1ሺህ 444 ሰዎች ሲሞቱ 3ሺህ 500 ያህሉ መቁሰላቸው የደማስቆ መንግስት እና የነፍስ አድን ሰራተኞች ገልጸዋል፡፡
በርዕደ መሬቱ ከሞቱትና ጉዳት ከደረሰባቸው በተጨማሪ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመት ማጋጠሙም የዓለም መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡
እናም የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል፡፡
በግንቦት ወር ለሚደረገው ከባድ ምርጫ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ርዕደ መሬቱ “ታሪካዊ አደጋ” ነው ማለታቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አደጋው እንደፈረንጆቹ ከ1939 ወዲህ በሀገሪቱ ላይ የደረሰ የከፋ አደጋ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የሰዎችን ህይወት ለማዳን መንግስታቸው ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ጥናት መረጃ እንደሚመለክተው ከሆነ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት ንዝረት በሌሎች የቱርክ ከተሞች እና በአካባቢው ባሉ ሀገራት ጭምር ተሰምቷል፡፡
ሶሪያ፣ ሊባኖስ እና ቆጵሮስ ርዕደ መሬቱ የተሰማባቸው ሀገራት ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ በሀገራቱ ላይ ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡
ቱርክ የምትገኝበት ካባቢ ለርዕደ መሬት ተጋላጭ መሆኑ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡