የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ኦባሳንጆ በካርቱም ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ
የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ጋር መወያየታቸው ይታወሳል
ኦባሳንጆ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል
በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር ተወያዩ፡፡
ሱዳን የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ወሳኝ አባል መሆኗን ያስታወሱት ኦባሳንጆ ከሉዓላዊ ምክር ቤቱ አመራሮች ጋር ለመምከር በማሰብ ወደ ሱዳን ማምራታቸውን ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ደህንነት፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ፖለቲካዊ ውይይት በማሳደግ ረገድ የሚጠቅሙ መሰረታዊ ሚናዎችን እንደምትጫወትም ነው የገለጹት፡፡
ሱዳን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የወቅቱ ሊቀመንበር ናት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የቀጣናዊው ተቋም ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የተቋሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚመራውም በሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርየም አል ሳዲቅ አል መህዲ ነው፡፡
ሆኖም ሱዳን በውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻዎች ትጠቀሳለች፡፡ በተለይም በሲቪል የለውጥ ኃይሎች እና በሃገሪቱ ወታደራዊ አመራሮች መካከል ያለው ልዩነት ከአል በሽር አገዛዝ መወገድ በኋላ የተጀመረውን የሽግግር ጉዞ እንዳያስተጓጉለው የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አለ፡፡
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ/ም ባለስልጣናቱ አክሽፈነዋል ያሉት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በሱዳን ተፈጽሞ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ላይ እንዳለም ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በይገባኛል የመሬት ጥያቄዎች በመወዛገብ ላይ ትገኛለች፡፡ ከውዝግብም አልፋ ኢትዮጵያ “ሉዓላዊ” የምትላቸውን መሬቶች ይዛለች፡፡
- የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ዙሪያ የሲቪል አስተዳድር ፖለቲከኞችን ወቀሱ
- “የግልበጣ ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው”- ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ
- የሱዳኑ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በሜ/ጄ አብደል ባቂ በክራዊ የተመራ ነው ተባለ
እነዚህን “ሉዓላዊ” መሬቶች “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለቃ እንድትወጣ”ም ነበር ኢትዮጵያ ስታሳስብ የቆየችው፡፡
ሱዳን በኢጋድ ያላትን ቀጣናዊ ሚና ተጠቅማ መንግስትን የተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከፈረጀው ህወሓት ጋርለማደራደር ያቀረበችው ጥያቄ “ተዓማኒነት ይጎድላታል” በሚል ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡
ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የሱዳንን ወሳኝነት ያነሱት ኦባሳንጆ አብሮ ለመስራት ዝግጁ ናቸው ካሏቸው የሃገሪቱ ባለስልጣናት እንዲሁም ከሌሎች የቀጣናው መሪዎች ጋር መምከር መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኦባሳንጆ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በዋናነት በኢትዮጵያ በተለይም ጦርነት ባለባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ሰብዓዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው በቅርቡ መሾማቸው የሚታወስ ነው፡፡