የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ ጥረት እያደረገ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ገለፀ
ህብረቱ፤ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ጉዳይ ከዋነኛ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን አስታውቋል
ከኢትዮጵያ ባሸገር በአፍሪካ ቀንድ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመፍታት ጥረቶች እያደረኩ ነው ብሏል
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት በመጨረሻ ወደ ጠረጴዛ ይመጣሉ የሚል ከፍተኛ ተስፋ እንዳለው የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ።
በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶየ ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ በህብረቱ በኩል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው” ብለዋል
- “በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች በኢትዮጵያ አመራርና በአፍሪካ ድጋፍ ይፈታል”- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረትን የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ሹመትን ተቀብላዋለች?
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት የአፍሪካ ህብረት ከመጀመርያው አንስቶ በትኩረት ሲከታተለው የነበረ ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናረዋል።
የግጭቱን መጠን ከግምት ውስጥ በማስገባት “በቅርቡ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ተደርገው መሾማቸው” ህብረቱ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክትም ገልጸዋል።
ህብረቱ በከፍተኛ ተወካዩ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየመከረ መሆኑንም ነው ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።
ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶየ አክለውም፤ እስካሁን እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች መሰረት “ሁሉም የግጭቱ ተዋናዮች በመጨረሻ ወደ ጠረጴዛ እንደሚመጡ ትልቅ ተስፋ አለን” ሲሉም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት አሁንም ቢሆን የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት እንዲፈታ በሶስት ቁልፍ ጉዳዮች እየመከረና በግጭቱ እየተሳተፉ ካሉ ኃይሎች ጋር እየተወያየ አንደሆነም ኮሚሽነሩ አክለው ጠቅሰዋል።
“ግጭቱን ማቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር ማድረግ እና ዘላቂ የሆነ ፖለቲካ መፍትሄ ማባጀት” የሚሉ ዓበይት ነጥቦች ህብረቱ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት እንዲቆም በተደጋጋሚ እና በቀጣይነት እየሰራባቸው የሚገኙ ናቸው ሲሉም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
ኮሚሽነሩ አክለውም ከኢትዮጵያ ባሸገር በአፍሪካ ቀንድ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ መሆናውንም አስታውቀዋል።
“የሶማሊያ ጉዳይ፣ የሱዳን እና ደቡብ ሱዳን አወዛጋቢው የአቢዬ ጉዳይ እንዲሁም የሱዳን የሽግግር ሂደት” ህብረቱ ዘለቂ መፍትሄ ለማበጀት እየሰራባቸው ካሉ አበይት የቤት ስራዎች እንደሆኑም ገልፀዋል።