የዩቲዩብ ቪዲዮ በመመልከት ቀዶ ጥገና ያደረገው "ሀሰተኛ ዶክተር”
የ15 አመት ታዳጊ ህይወቱ እንዲያልፍ ምክንያት የሆነው ግለሰብ ጠፍቶ በፖሊስ እየታደነ ነው
በህንድ የህክምና እውቀትና ልምድ ሳይኖራቸው “ዶክተር ነን” የሚሉ ግለሰቦች እየተበራከቱ ይገኛሉ
በህንድ የዩቲዩብ ቪዲዮ እየታገዘ የቀዶ ጥገና ያደረገው “ዶክተር” በፖሊስ እየተፈለገ ነው።
በቢሃር ግዛት ሳራን በተባለች ከተማ በጋንፓቲ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰራው አጂት ኩማር ፑሪ የ15 አመት ታዳጊ ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።
ታዳጊው ባለፈው ሳምንት ደጋግሞ ሲያስመልሰው ነበር ዶክተር ፑሪ ወደሚሰራበት ሆስፒታል ወላጆቹ የወሰዱት።
ዶክተር ፑሪ ማስታገሻ ወስዶ ማስመለሱ የቆመለት ታዳጊ የሃሞት ጠጠር የህመሙ መነሻ ነው በሚል ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል ማለቱ አስደነገጠን የሚሉት የልጁ ወላጆች፥ ስንከራከርም በሃይለቃል ተቆጥቶ ከህክምና ክፍሉ አስወጣን ሲሉ ለኤንዲቲቪ ተናግረዋል።
- የታዳጊው ወላጆች ጭንቀታችን ከምንም ሳይቆጥር ያለፈቃዳችን ቀዶ ህክምናውን አድርጓል ሲሉም ከሰዋል።
“ልጄ ሆስፒታል ውስጥ እንደገባ ማስመለሱ ቢቆምለትም ዶክተር ፑሪ ቀዶ ጥገና ማድረግ አለበት አለ፤ እናም የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን እየተመለከተ ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ ሞከረ፤ ደህና የነበረው ልጃችን እየባሰበት ሄዶ ህይወቱ አለፈ” ብለዋል ስማቸው ያልተጠቀሰው የታዳጊው አባት።
ከቀዶ ጥገናው በኋላ ትንፋሹ መቆራረጥ የጀመረውን ታዳጊ ወደ ሌላ ሆስፒታል እንዲወስዱት ያሳሰበው ዶክተር ፑሪ፥ በጭንቅ ለነበሩት ወላጆች “እናንተ ዶክተር ብትሆኑ ምን ታደርጋላችሁ?” በሚል ጥያቄያቸውን በጥያቄ መመለሱም ተጠቅሷል።
ታዳጊው ወደ ሌላ ሆስፒታል እየተወሰደ እያለ ህይወቱ ማለፉን የገለጹት ቤተሰቦቹ፥ ወደ ሆስፒታሉ ሲመለሱ ዶክተር ፑሪ ደብዛውን ማጥፋቱን ለፖሊስ አስረድተዋል።
የታዳጊው ወላጆች የዶክተር ፑሪ መሰወር ምናልባትም ሃሰተኛ ሀኪም መሆኑን ሊያመላክት እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፥ ፖሊስም ምርምራውን መቀጠሉን ኦዶቲ ሴንትራል አስነብቧል።
በህንድ “ዶክተር” ነን የሚሉና በሀሰተኛ ማስረጃ በሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦች ሲጋለጡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
በዚህ አመት መጀመሪያ በሙምባይ ባል በሚስቱ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ሲያክም ተገኝቶ ነበር።
ከአራት አመት በፊትም ከአምስተኛ ክፍል ያቋረጠው ወጣት ለአራት አመታት በ16 ሆስፒታሎች ውስጥ “ዶክተር” እየመሰለ ሲሰራ ቆይቶ በመጨረሻም እንደተደረሰበት ዘገባው አስታውሷል።