ፖሊስ መስሎ ለተፈታኝ እህቱ “አጤሬራ” ለማቀበል የሞከረው ህንዳዊ ተያዘ
የ24 አመቱ ወጣት ወደ መፈተኛ ክፍል ተቆጣጣሪ መስሎ ለመግባት ሲሞክር አለባበሱና ሁኔታው ግራ ባጋባቸው ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውሏል
በህንድ ብሄራዊ ፈተናዎች ሲቃረቡ የኩረጃ፣ ለሌላ ሰው የመፈተንና ፈተናዎችን ሰርቆ የማውጣት ሙከራዎች ይበራከታሉ
የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ እህቱን ለመርዳት ወደ ፈተና መስጫ ጣቢያ ፖሊስ መስሎ ያመራው ህንዳዊ በቁጥጥር ስር ዋለ።
በማሃራሻትራ ግዛት ፓቱር በተባለችው ከተማ ነዋሪ የሆነው የ24 አመቱ አኑፓም ማዳን ካንዳሬ ካኪ የፖሊስ መለዮ ልብሱን አድርጎ ሻባቡ ኡርዱ ወደተሰኘው ትምህርት ቤት መግባት ችሏል።
እቅዱም የፈተና ተቆጣጣሪ መስሎ ስሟ ላልተጠቀሰው እህቱ በአጫጭር የተጻፉ ማስታወሻዎችን ወይም “አጤሬራ” በማቀበል ፈተናውን እንድታልፍ መርዳት ነበር።
የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ አልፎ ወደ ፈተና ክፍሎች በማምራት ላይ እንዳለ ግን ያልተዘጋጀበት ጉዳይ ገጠመው።
ትክክለኞቹ ፖሊሶች ተሰብስበው የፈተናውን ደህንነት ለማስጠበቅ ምክክር ሲያደርጉ ፊት ለፊት ተመለከታቸው።
“ሀሰተኛው ፖሊስ” ካንዳሬ ምክክር ላይ በማድረግ ላይ የነበሩትን ፖሊሶች እየተዘዋወረ ሰላምታ በመስጠት ባልደረባቸው ለመምሰል ያደረገው ጥረት ግን ጥርጣሬ ውስጥ ከተተው።
ሰላምታ አሰጣጥ እና አለባበሱ ያጠራጠራቸው ፖሊሶች ሲመረምሩትም ስም የሚጻፍበት ባጅ እና የመለዮ ልብሱ ጥራት ከትክክለኛው ዩኒፎርም የተራራቀ መሆኑን ይደርሱበታል።
ኪሶቹን ሲፈትሹትም ለ12ኛ ክፍል ተፈታኝ እህቱ ሊያቀብላት ያዘጋጃቸው “አጤሬራዎች” ተገኝተዋል።
የ24 አመቱ የሀሰት ፖሊስ ወዲያው በቁጥጥር ስር ውሎም ዘብጥያ የወረደ ሲሆን፥ በተደራራቢ የወንጀል ክሶች የሚተላለፍበትን ቅጣት እየተጠባበቀ ነው ብሏል ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው።
በህንድ በተማሪዎች መጻኢ ትልቅ ትርጉም በሚሰጣቸው ብሄራዊ ፈተናዎች ወቅት ኩረጃ፣ ተመሳስሎ በመግባት ለሌላ ሰው መፈተን እና ፈተናን አስቀድሞ የመስረቅ ሙከራዎች ተደጋግመው ይታያሉ።
ከአንድ ወር በፊትም ሴት መስሎ (ቀሚስ ለብሶ፤ የአጅ አንባር አድርጎ፤ የሴቶች ቦርሳ ይዞና ከንፈሩንም ቀለም ተቀብቶ) ለፍቅረኛው ፈተና ለመፈተን የገባው ህንዳዊ በቁጥጥር መዋሉን መዘገባችን ይታወሳል።