የቀልድ አስመስሎ የምር ሚስት ያገባው ሰው በመጨረሻም ትዳሩ ፈረሰ
ግለሰቡ አዲስ ተጋቢዎች መስለን ቪዲዮ እንስራ በሚል ያሳመናትን ሴት የምር አግብቷል
አታሎኛል ያለችው ሚስትም ረጅም ጊዜ በፈጀ ክርክር ትዳሩ እንዲፈርስ አስደርጋለች
የቀልድ አስመስሎ የምር ሚስት ያገባው ሰው በመጨረሻም ትዳሩ ፈረሰ፡፡
በአውስትራሊያ ይኖራሉ የተባሉት ሰዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት ነበር ትውውቀቸው የጀመረው፡፡
በሜልቦርን እና ሲድኒ ከተሞች የሚኖሩት እነዚህ ሰዎች ቀስ በቀስ ወዳጅነታቸውን ወደ ፍቅር ይቀይሩታል፡፡
ወንዱ በኢንስታግራም ቪዲዮዎችን ለተከታዮቹ በማጋራት የሚታወቅ ሲሆን ለየት ያለ ነገር ማድረግ እንደሚፈልግ እቅድ ያወጣል፡፡
ለዚች ጓደኛውም የኢንስታግራም ገጽ ተከታዮቹን ለማሳደግ በሚል የተጋባን እስመስለን ቪዲዮ እንቀረጽ እና ላጋራ ሲልም ጥያቄ ያቀርብላታል፡፡
ይህን የሚያደርገውም የኢንስታግራም ተከታዮቹ እንዲያድግለት እና የተሻለ ገቢ ከመተግበሪያው ለማግኘት እንደሆነም ያሳምናታል፡፡
ጓደኛዋን ለመርዳት በሚል ቪዲዮውን ለመቀረጽ የተስማማችው ይህች ሴትም ሁነቱ የእውነት እንዲመስል የተባለችውን ሁሉ እያደረገች ትቀረጻለች፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ከዜግነት ጋር የተያያዘ አገልግሎት ለማግኘት ስትሞክር ግን የባሏንም ስም እንድትጠቅስ ይነገራታል፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር ለቀልድ ተብሎ የተደረገው ዝግጅት የምር ትዳር እንደመሰረተች እና ባልም እንዳላት የተረዳችው፡፡
ባል የተባለው ጓደኛዋን ስለጉዳዩ ስታወራውም ይህን ያደረገው የአውስትራሊያ ዜግነት ለማግኘት ሲል እንደሆነ ይነግራታል፡፡
በድርጊቱ ማዘኗን የምትናገረው ይህች ሴትም ትዳሩ በህጋዊነት ስለተመዘገበ የግድ በፍርድ ቤት እንዲፈርስላት ለማመልከት መገደዷን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
ባልየውም ለፍርድ ቤቱ ሚስቱን በህጋዊ መንገድ ማግባቱን፣ ለዚህም የእሷ እውቅና እና ፈቃደኝነት እንዳለበት ይናገራል፡፡
ባልየው ከፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ጋብቻው ስትፈጽሙ ለምን ቤተሰቦቻችሁ ባለበት አላደረጋችሁም፣ አብራችሁስ መኖር ለምን አልቻላችሁም የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ባለመቻሉ ከረጅም ጊዜ ክርክር በኋላ ጋብቻው እንዲፈርስ ውሳኔ ተላልፏል፡፡