አዙሪዎቹ በሰሜን መቄዶንያ ተሸንፈው ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውጭ መሆናቸው ይታወሳል
ጣሊያን ከ2022ቱ የዓለም ዋንጫ ውጭ መሆኗን ተከትሎ በአዙሪዎቹ ቤት ሃዘን ነግሷል፡፡
አዙሪዎቹ በሰሜን መቄዶንያ ተሸንፈው ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውጭ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
ሰሜን መቄዶንያ በአሌክሳንደር ትራጅኮቪስኪ ብቸኛ የመጨረሻ ሰዓት ጎል ነው የጨዋታውን አስተናጋጅ ጣሊያንን ያሸነፈችው፡፡ ትራጅኮቪስኪ በ92ኛው ደቂቃ ጣሊያንን ያሰናበተችውን ጎል አስቆጥሯል፡፡
በዚህም ባሳለፍነው ክረምት ሻምፒዮን ሆና የአውሮፓ 2020 ዋንጫን ያነሳችው ጣሊያን በማጣሪያ ጨዋታው ከዓለም ዋንጫው ውጭ ሆናለች፡፡
ይህ በተከታታይ ሁለት የዓለም ዋንጫዎች የሆነ ነው፡፡ የ2006ቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጣልያን በተመሳሳይ መልኩ ከ2018ቱ የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ውጭ መሆኗ ይታወሳል፡፡
ጣሊያንን ያሸነፈችው ሰሜን መቄዶንያ በዓለም የሃገራት የእግር ኳስ ደረጃ 67ኛ ነች፡፡
በዚህ ማዘናቸውንና ልባቸው መሰበሩን ተጫዋቾች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ጠባሳው አብሮን ይዘልቃል ያለው የጁቬንቱሱ ተከላካይ ጆርጂዮ ቼሊኒ የተሻልን የነበርን ቢሆንም የጎል እድልን ለመፍጠር አልቻልንም ብሏል፡፡ በወርሃ መስከረም ከነበሩ ጨዋታዎች ጀምሮ ስህተቶችን መስራታቸውን ያስታወሰው ቼሊኒ በዚህም የእጃችንን አግኝተናል ብሏል የማይሽር ጠበሳ መሆኑን በመጠቆም፡፡
የቼልሲው ተጫዋች ጆርጊንሆም ከአሁን ቀደም ያመከናቸው የፍጹም ቅጣት ምት እድሎች ሃገሩን ከዓለም አቀፉ ውድድር ውጭ ከመሆን ይታደጉ እንደነበር በማስታወስ በሁኔታው ማዘኑን ገልጿል፡፡ ሁልጊዜ ሲያስታውሰው የሚኖር መጥፎ አጋጣሚ መፈጠሩንም ነው ጆርጊንሆ የተናገረው፡፡ ተጫዋቹ ከስዊዘርላንድ አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት እድሎችን ስቷል፡፡ ጨዋታው ማጣሪያውን ማለፋቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉበት ነበር፡፡
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በሩሲያ እንዳይደረግ ተወሰነ
በሮበርት ማንቺኒ የሚሰለጥኑት አዙሪዎቹ ከአሁን ቀደም ካደረጓቸው 5 የማጣሪያ ጨዋታዎች በ4ቱ አቻ ወጥተዋል፡፡ ይህ መሆኑ ምድባቸውን በመሪነት እንዳያጠናቅቁ አድርጓል፡፡ በስተመጨረሻም ከሰሜን መቄዶንያ ጋር በፓሌርሞ ያደረጉትን ጨዋታ በጠባብ ውጤት ተሸንፈው ከጨዋታው ውጨ ለመሆን ተገደዋል፡፡
ይህ የጣሊያን ሊግ (ሴሪ ኤ) ነጸብራቅ መሆኑ ጭምር ነው የተነገረው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጣሊያን እግር ኳስ ማሳያ የሆኑት የሴሪ ኤው ተሳታፊ ክለቦች ተዳክመው መታየታቸው ይነገራል፡፡
ጁቬንቱስ እና ኢንተር ሚላን ገና ጥሎ ማለፉን ሳይቀላቀሉ ነው ከዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሰናበቱት፡፡ ኤሲ ሚላንና አትላንታ ደግሞ ከምድባቸው እንኳ ለማለፍ አልቻሉ፡፡ በጆዜ ሞውሪንሆ ይሰለጥን የነበረው ኢንተር የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካነሳበት ከ2010 ወዲህ ዋንጫውን ማንሳት አይደለም ለፍጻሜ ተፋላሚነት የበቃ የሴሪ ኤ ቡድንም የለም፡፡
የሴሪ ኤው አስተዳዳሪ አካል ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች የተጣጣመ የጨዋታ ሰሌዳ እንዲኖረው ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች አዙሪዎቹን ዋጋ እንዳስከፈሉም ይነገራል፡፡ አጠቃላይ እግር ኳሳዊና ተቋማዊ ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉ ድምጾች እየተሰሙም ነው፡፡