ሮናልዶ ሃት-ትሪክ ሲሰራ በእግር ኳስ ህይወቱ ለ62ኛ ጊዜ መሆኑ ነው
ሮናልዶ ለሳኡዲው ክለብ አል ናስር ሁለተኛውን ሃት-ትሪክ ሰርቷል፡፡
ሮናልዶ ሃት-ትሪክ የሰራው ክለቡ አል-ናስር ከዳማክ ጋር በነበረው ጨዋታ ሲሆን ሶስቱም ጎሎችን ከእረፍት በፊት በነበረው ጨዋታ በማስቆጠር ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል፡፡
የ38 አመቱ ሮናልዶ ጎሎቹን ሊያስቆጥር የቻለው አንዱ በፍጹም ቅጣት ምት እንዲሁም ሁለቱ በጨዋታ ነው፡፡
ለአል ናስር ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው ሮናልዶ ፤ አሁን ላይ በሳኡዲ ፕሮፌሽናል ሊግ የአል-ሸባብ ክለብ ተጨዋች ከሆነው ካርሎስ ጁኒየር ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን እንደቻለም ነው የደይሊ ሜይል ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
ሮናልዶ ሃት-ትሪክ ሲሰራ በእግር ኳስ ህይወቱ ለ62ኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
የቀድሞው የሪያል ማድሪድ እና የጁቬንቱስ የፊት መስመር ተጫዋች ከዚህ ቀደም በነበረው አንድ ጨዋታ ጎል ባያስቆጥርም 90 ደቂቃ ሙሉ ተጫውቶ ሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡
በቅርቡ 38ኛ ልደቱን ያከበረው ሮናልዶ በቅርቡ ክለቡ አል-ናስር ከአል-ዌህዳ ጋር በነበረው ጨዋታ አራት ጎሎችን በማስቆጠር ሃት-ትሪክ ሰርቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይህም ሮናልዶ በሌሎች ሊጎች ላይ ያሳየውን ድንቅ ችሎታ በሳኡዲ የመድገም አቅም ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው ተብሏል፡፡
ሮናልዶ ለአል-ናስር የሚጫወተው እስከ 2025 ክረምት ድረስ መሆኑ ይታወቃል፡፡