አዲስ የተመሰረተው የጣሊያን ው መንግሥት ለሩሲያ ቅርብ እንዳይሆን ተሰግቷል
ጆርጂያ ሜሎኒ የጣልያን የመጀመሪያዋ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን በዛሬው እለት ተሹመዋል።
በስልጣን ላይ ያሉት የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ማቲዮ ድራጊ በሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት መተማመኛ ድምጽ ማጣታቸውን ተከትሎ በጣልያን ዳግም ምርጫ መካሄዱ ይታወሳል።
በዚህ ምርጫ ላይ የጣልያን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የምክር ቤቱን አብላጫ ወንበሮች ማሸነፋቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አዲስ መንግሥት እንዲመሰረት ፈቃድ ሰጥተዋል።
ይሄንን ተከትሎም ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ለተሾሙት ጆርጅያ ሜሎኒ ካቢኔያቸውን እንዲያዋቅሩ ማዘዛቸውን ተከትሎ ዛሬ በሮም አዲስ መንግሥት ተመስርቷል።
የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርልስኮኒ የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አንቶኒዮ ታጃኒ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
አዲሱ የጣልያን መንግስት በ19 ሚንስትሮች እንደሚዋቀር ሲገለጽ ዘጠኙ ለጣልያን ብራዘርስ ፓርቲ፣ አምስቱ ለፎርዛ ኢጣልያ ፓርቲ እንዲሁም አምስቱ ደግሞ ለባለሙያዎች ይሰጣል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
አዲስ የተመሰረተው መንግስት በቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የበላይነት የሚመራ ሲሆን ይህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ጆርጂያ ሜሎኒ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ አዲስ የሚመሰርቱት መንግስት ከኔቶ እና አውሮፓ ህብረት ጋር ተናቦ የሚሰራ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በምርጫው ከብራዘርስ ኢጣሊያ በመቀጠል ብዙ የምክር ቤት መቀመጫ ያገኘው እና በቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርልስኮኒ የሚመራው ፎርዛ ኢጣልያ ፓርቲ በበኩሉ ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው ይታወቃል።
አዲስ የሚዋቀረው የጣልያን መንግስት የኔቶ እና ሩሲያ ጥላ እንዳያጠላበት የተሰጋ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና ሌሎች ፈተናዎችም አሉበት።