ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ ሞተር የተገጠመለት አውሮፕላኑ 115 የፈረስ ጉልበት አለው
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው "ፀሐይ" የሚል መጠሪያ የተሰጠው አውሮፕላን በዛሬው እለት ከጣሊያን ለኢትዮጵያ ተመለሶ ተሰጠ።
በጣሊያን ተወስዶ የነበረው አውሮፕላኑ በዛሬው እለት ለኢትዮጵያ ተመልሶ መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ዛሬ "ፀሐይ" አውሮፕላንን ከጣልያን መንግሥት በይፋ መረከባችንን የምናከብርበት ቀን በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ታላቅ የኩራት ቀን ነው” ብለዋል።
“የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኔ ላለፈው አንድ አመት የአውሮፕላኑን መመለስ ስራ በማገዛቸው ለማመስገን እፈልጋለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።
"ፀሐይ" በኢትዮጵያ የተሰራው የመጀመሪያው አውሮፕላን አውነታዎች
"ፀሐይ" በ1935 ዓ.ም ሄር ሉድዊግ ዌበር የተባለው ጀርመናዊ ኢንጂነር እና የንጉሱ ፓይለት በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተሰራ የመጀመሪያው አውሮፕላን ነው።
አውሮፕላኑ "ፀሐይ" የሚለውን ስያሜውም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ የተሰጠ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፀሐይ ባለሁለት መቀመጫ እና ሁለትዮሻዊ መቆጣጠሪያ ያለው ብሎም የባለከፍተኛ ኃይል ሞተር ባለቤት ተደርጎ የተሰራ አውሮፕላን ነበር።
"ፀሐይ" ኮምፓስ፣ የአብራሪ መቆጣጠሪያዎች፣ ሁለት ያለ ፍሬን ማቆሚያ የተገጠሙ የማረፊያ ሽክርክሪቶች የነበሩትም ነበር።
ሞተሩ ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ ሲሆን የውሃ ማቀዝቀዣ ስርዓት የነበረው የ115 የፈረስ ጉልበት ባለቤትም ነበር።
"ፀሐይ" ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ የተሰራ ብቸኛ አውሮፕላን ነው።
ፀሐይ በውስን ሃብት እና ስፍራ በጊዜው የነበሩትን አናፂዎች እውቀት እና የእጅ ጥበብ በመጠቀም የተሰራ አውሮፕላን ሲሆን የ1930ዎቹ የአቪየሽን ጥረት ማሳያ ሆኖ የተረፈን አውሮፕላን ነው።