የህክምና ባለሙያዎች ናቸው የተባሉት ዘጠኝ ተሳፋሪዎችም በአልሻባብ እጅ ወድቀዋል ተብሏል
ንብረትነቱ የተመድ የሆነ አውሮፕላን በአልሻባብ እጅ ወደቀ።
ንብረትነቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሆነ አነስተኛ አውሮፕላን በማዕከላዊ ሶማሊያ በአልሻባብ እጅ እንደወደቀ ተመድ አስታውቋል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ እንዳሉት አውሮፕላኑ ከሶማሊያዋ ቤልድወንይ ወደ ጋልሙዱግ በመጓዝ ላይ እያለ የቴክኒክ ብልሽት አጋጥሞታል።
ዘጠኝ የህክምና ባለሙያዎችን አሳፍሮ እየተጓዘ የነበረው ይህ አነስተኛ አውሮፕላን በብልሽት ምክንያትም አውሮፕላኑ ተገዶ በማዕከላዊ ሶማሊያ ሽንዲሬ በተሰኘች ስፍራ ሊያርፍ ችሏል ተብሏል።
የአልሻባብ ታጣቂዎችም ወዲያውኑ ይህን አነስተኛ አውሮፕላኑን እንደተቆጣጠሩ እና ተሳፋሪዎቹን አግተው እንደወሰዱ ተገልጿል።
ታጣቂዎቹ ወዲያውኑ አውሮፕላኑን አቃጥለውታል የተባለ ሲሆን ስለታጋቾቹ እስካሁን ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ ቪኦኤ ዘግቧል።
ተመድ በአውሮፕላኑ ላይ የነበሩ ሰራተኞቹን ማንነት ለደህንነታቸው በመስጋት ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
በታጣቂዎቹ የተያዙትን የተመድ ሰራተኞች ለማስለቀቅ ጥረቶች እየተካሄዱ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ይህ አነስተኛ አውሮፕላን የቆሰሉ ሰዎችን ወደ ህክምና ቦታ ለመውሰድ አልሞ በረራ እንደጀመረም ተገልጿል።
ተመድ በአፍሪካ ህብረት ስር ለተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሀይል የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።