በቀን ለ16 ሰአት ከምግብ መራቅ ለልብ ህመምና ስትሮክ ተጋላጭነትን በእጥፍ ይጨምራል - ጥናት
ለረጅም ስአት ከምግብ መራቅ ክብደትን ለመቀነስ ሊያግዝ ቢችልም የረጅም ጊዜ የጤና ጉዳቱ ግን አሳሳቢ መሆኑን የሚያሳይ ጥናት ይፋ ተደርጓል
ጥናቱ ለረጅም ስአት ከምግብ ርቆ አብዝቶ ከመመገብ በስአታት ልዩነት በመጠኑ መመገብ የተሻለ ነው ብሏል
በ24 ስአት ውስጥ ለረጅም ስአት ከምግብ ርቆ በተወሰኑ ስአታት ውስጥ የመመገብ ልማድ ከሆሊውድ መንደር እስከ ለንደኑ ዳውኒንግ ስትሪት እየተለመደ መጥቷል።
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ፣ ቢሊየነሩ ኤለን መስክ፣ ተወዳጇ ተዋናይ ጀኒፈር አኒስተንን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች አመጋገባቸውን በስአታት ውስጥ መገደባቸው ጤናማ እና ሸንቃጣ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ ይደመጣል።
በ24 ስአት ውስጥ ከአራት እስከ 12 ስአታት ምግብ ባለበት ላለመገኘት ለራሳቸው ቃል ገብተው ካስቀመጡት የጊዜ ገደብ ውጭ የማይመገቡ ሰዎች ባለፉት አመታት እየተበራከቱ መሄዳቸው ይነገራል።
ይህ በጊዜ የተገደበ አመጋገብም የደም ግፊት እና ጎጂ ኮሊስትሮል መጠንን ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ የተለያዩ ጥናቶች አመላክተዋል።
በ24 ስአት ውስጥ ከተወሰኑ ስአታት ውጭ ቀሪውን ከምግብ የመራቅ ልማድ በተከተሉ ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች የተደረገ አዲስ ጥናት ግን ከቀደሙት ጥናቶች የተለየ ውጤት አሳይቷል።
በቀን ውስጥ 16 ስአት እና ከዚያ በላይ ከምግብ መራቅ ለልብ ህመም እና ስትሮክ የመጋለጥ እድልን በእጥፍ ይጨምራል ብሏል በአሜሪካ የልብ ማህበር የ2024 ጉባኤ የቀረበ ጥናት።
በጥናቱ የተካተቱት ሰዎች በ24 ስአት ውስጥ ለ16 ስአት ከምግብ ርቀው በቀሪው 8 ስአት ውስጥ የሚመገቡ ናቸው።
ከፈረንጆቹ 2003 - 2018 ይፋ የተደረጉ አመታዊ የጤና ዳሰሳዊ ጥናቶች መሰረት ያደረገው ጥናት አብዛኞቹ ይህን የአመጋገብ ስርአት የሚከተሉ ሰዎች ለልብና ተያያዥ ህመሞች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ መሆኑን አሳይቷል ነው የተባለው።
በ12 ስአት ልዩነት ከምግብ ጋር ከሚገናኙ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩም በልብ ህመም የመሞት እድላቸው በእጥፍ እንደሚጨምር የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ኬት ፍርያን ይናገራሉ።
“ለረጅም ስአት መጾም ሰውነታችን ምግብ ለመፍጨት የሚጠቀመውን ካሎሪ ለመቀነስ እንደሚያግዝና ሌሎች በርካታ በረከቶች እንዳሉት የሚናገሩ ሰዎች ቢበዙም ያደረግነው ጥናት አሳሳቢ ጉዳዮችም ያመላከተ ነው” ሲሉም በቀጣይ ሰፊ ምርምር ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በለንደን ኪንግ ኮሌጅ የስርአተ ምግብ ፕሮፌሰር የሆኑት ቶም ሳንደርስም ለረጅም ስአት ከምግብ ከመራቅና በመመገቢያ ስአት አግበስብሶ ከመብላት ይልቅ በጥቂት ስአት ልዩነት መጠነኛ ምግብ መመገብ የተሻለ ውጤት ያስገኛል ባይ ናቸው።
ከዚህ ቀደም የተደረጉት ጥናቶችም ለረጅም ስአት መጾም ክብደትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ቢጠቁሙም አሳማኝ ማስረጃዎችን ማቅረብ አልቻሉም ሲሉ ተከራክረዋል።
በዚህ ሳምንት ይፋ የተደረገው ጥናት በቀጣይ ለሚደረጉ ምርምሮች በር ከፋች ነው ተብሏል።