የኢራኑ መሪ ኢብራሂም ራይሲ ኢራን ጥቃት በማድረስ በተጠረጠረችው እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ ትወስዳለች ብለዋል
ኢራን በሶሪያ ደማስቆ በሚገኘው ኢምባሲዋ ላይ ጥቃት ያደረሰችውን እስራኤልን እበቀላለሁ የሚል ዛቻ አሰምታለች።
የኢራኑ መሪ ኢብራሂም ራይሲ ሰባት የኢራን ወደራዊ አዛዦች የተገደሉበት ጥቃት ከተፈጸመ ከአንድ ቀን በኋላ ኢራን ጥቃት በማድረስ በተጠረጠረችው እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ ትወስዳለች ብለዋል።
"በግንባር የገጠመውን መከላከል መስበር ያልቻለው ጽዮናዊው መንግስት፣ ራሱን ለማዳን የዘፈቀድ ጥቃትን አጀንዳው አድርጓል። ግቡን ማሳካት አንደማይችል እና እንዲህ አይነት ጥቃቶች ዝም ተብለው እንደማይታለፉ ማወቅ አለበት" ብለዋል ራይሲ።
እስራኤል በሶሪያ ውስጥ የሚገኙ የኢራን ወታደራዊ ቦታዎችን እና አጋሮቿን ስትመታ የቆየች ቢሆኖም፣ በትልቅ የኢምባሲ ግቢ ላይ ጥቃት ስትፈጽም ይህ የመጀመሪያዋ ነው።
በዚህ ጥቃት የኢሊት ኩድስ ፎርስን ሲመሩ የነበሩት ጀነራል መሀመድ ሬዛ ዛኸዲ መገደላቸውን የኢራን ሪቮሉሽነሪ ጋርድ አስታውቋል። የዛኸዲ ምክትል ጀነራል ሀዲ ሀጂራሂሚ እና ሌሎች አምስት ሰራተኞችም በጥቃት ተገድለዋል።
የሄዝቦላ አባል የሆነው ሁሴን የሱፍ በጥቃቱ መገደሉን ኤፒ ዘግቧል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ናስር ከናኒ ሀገራት ይህን ጥቃት እንዲያወግዙት ጠይቋል።
እስራኤል አደረሰችው በተባለው ጥቃት ጉዳይ አስተያየት አልሰጠችም።
እስራኤል በጋዛ ለምትዋጋው ሀማስ አጋርነታቸውን ላሳዩት የሊባኖሱ ሄዝቦላ እና የየመኑ ሀውቲ ታጣቂ ቡድኖች ድጋፍ በማድግ ኢራንን ትከሳለች።