ተቃውሞ የወጡ እስራሌላውያን በጋዛ ታግተው የሚገኙ እስራኤላውያን እንዲለቀቁ ጠይቀዋል
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ተቃውመው በእየሩሳሌም አደባባይ ወጥተዋል።
በእየሩሳሌም በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ እስራኤላውያን በጋዛ የታገቱ እስራኤላወያን እንዲለቀቁ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል ነው የተባለው።
ተቃዋሚዎች በትናንትናው እለት ምሽት ላይ ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ ዋናውን መንገድ የዘጉ ሲሆን፤ በእስራኤል ፓርላማ ፊትለፊት ባደረጉት ሰልፍ ላይ ባንዲራ እያውለበለቡ እሳት ሲያቀጣጥሉ ታይተዋል።
ሰልፈኞቹ በትናንትናው እለት የተካሄደው ሰልፍ የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ትልቁ እንደሆነም ነው ያስታወቁት።
“ሰልፈኞቹ ኔታንያሁ መልቀቅ አለበት” የሚል መፈክር ማሰማት በሚጀምሩበት ጊዜም ፖሊስ በውሃ በመጠቀም ሰልፈኞች ወደኋላ እንዲመለሱ ማድረግ መጀመሩ ተነግሯል።
በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ተቃውሞዎች እና ጫናዎች እየበረቱ መጥተዋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ጦርነት ከመክፈቷ በፊትም ከፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ላይ የተቃውሞ ሰልፎች እየተደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ 250 ሰዎችን ማገቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 130 ሰዎች አሁንም በሃማስ እጅ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 33ቱ ሳይሞቱ አልቀረም ተብሏል።
እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ 32 ሺህ 782 ፍሊስጤማውያን መሞታው የሚታወቅ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻት መሆናቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።