የፓኪስታን የኒኩሌር አባት አብዱልቃድር ከሃን ህወታቸው አለፈ
አብዱልቀድር ከሃን ፓኪስታን የኒኩሌር የጦር መሳሪያን የታጠቀች የመጀመሪያዋ እስላማዊ ሀገር ማድረግ የቻሉ ናቸው
ተመራማሪው የኒኩሌር ቴክኖሎጂን ለሰሜን ኮሪያ፣ ኢራንና ሊቢያ አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል በምእራባውያን ዘንድ ይተቻሉ
የፓኪስታን የኒኩሌር መርሃ ግብር አባት እና መሃዲስ በመባል የሚታወቁት ተመራማሪው አብዱልቀድር ከሃን ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።
አብዱልቀድር ከሃን በህመም ምክንያት በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የፓኪስታን ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው ቢቲቪ ዘግቧል።
ፓኪስታናዊው የኒኩሌር ተመራማሪ አብዱልቀድር ከሃን የሀገሪቱ ብሄራዊ ጀግና ተደርገው ነው በበርካቶች የሀገሪቱ ዜጎች ዘንድ የሚታዩት።
ምንያቱ ደግሞ አብዱልቀድር ከሃን ፓኪስታን የኒኩሌር የጦር መሳሪያን የታጠቀች የመጀመሪያዋ እስላማዊ ሀገር እንድትሆን ማድረግ በመቻላቸው ነው ተብሏል።
አብዱልቀድር ከሃን የፓኪስታን የመጀመሪያው የኒኩሌር ማብላያ ጣቢያ በኢስላማባድ አቅራቢያ እንዲተከል ማድረግ የቻሉ ሲሆን፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ1998 ሀገሪቱ የመጀመሪያውን የኒኩሌር የጦር መሳሪያ ሙከራ እንድታደርግም አስችለዋል።
ተመራማሪው አብዱልቀድር ከሃን የኒኩሌር ቴክኖሎጂን በህገ ወጥ መንገድ ለሰሜን ኮሪያ፣ ኢራን እና ሊቢያ አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል በምእራባውያን ዘንድ ይተቻሉ።
አብዱልቀድር ከሃን ከሳምባ ህመም ምክንያት ሆስፒታል ገብተው ህክምና ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በ88 ዓመታው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል።
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሃን በተመራማሪው አብዱልቀድር ከሃን ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን የገለጹ ሲሆን፤ ፓኪስታን አንድ ቁልፍ የሆነ ሰው አጣች” ብለዋል።
“አብዱልቀድር ከሃን በሀገሪቱ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አላቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሃን፤ “ምክንያቱ ደግሞ ፓኪስታንን ኒኩሌር የታጠቀች ሀገር ማድረግ በመቻላቸው ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባስተላፉት መልእክት አስታውቀዋል።