አሜሪካ የጎግልን ቁልፍ ሚስጥሮች ለቻይና ሲያስተላልፍ የነበረውን ባለሙያ መያዟን ገለጸች
ሰራተኛው በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቁልፍ መረጃዎችን ለቻይና አሳልፎ ሰጥቷል ተብሏል
በኤፍቢአይ የተያዘው ይህ ሰራተኛ ጎግል ኩባንያ አሉኝ የሚላቸውን መረጃዎች ለቻይና ተፎካካሪ መረጃዎች አስላልፎ መገኘቱ ተገልጿል
አሜሪካ የጎግልን ቁልፍ ሚስጥሮች ለቻይና ሲያስተላልፍ የነበረውን ባለሙያ መያዟን ገለጸች፡፡
ሊንዊ ዲንግ የተሰኘው የጎግል ሰራተኛ የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሙያ ሆኖ የተቀጠረው ከአራት ዓመት በፊት ነበር፡፡
የሶፍትዌር ኢንጅነር ሙያተኛ የሆነው ይህ ሰራተኛ ጎግል የሚያከናውናቸውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ ልውውጦችን በቻይና ላሉ ሁለት ተቋማት ማስተላለፉ ተገልጿል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ሰራተኛው በአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ወይም ኤፍቢአይ የተያዘ ሲሆን የድርጅቶችን ከፍተኛ ሚስጥሮች አሳልፎ በመስጠት ወንጀል ተከሷል ተብሏል፡፡
ይህ ባለሙያ በፈጸመው የቴክኖሎጂ ስርቆት እስከ 10 ዓመት እስር ሊወሰንበት እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡
የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ራይ እንዳሉት “የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የአሜሪካንን ቴክኖሎጂ እንደሚሰርቁ ይህ ትክክለኛ ማስረጃ ነው” ብለዋል፡፡
የጎግል እናት አልፋቤት ኩባንያ 166 ቢሊዮን ዶላር መክሰሩ ተገለጸ
ቻይና በምታካሂዳቸው የቴክኖሎጂ ስርቆቶች ምክንያት በርካታ አሜሪካዊያን የስራ እድል ሲያጡ ኩባንያዎች ደግሞ ከገበያ እና ውድድር ውጪ እንደሚሆኑም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የጎግል ኩባንያ ቃል አቀባይ ጆሴ ካስታኔዳ በበኩላቸው ጎግል ቁልፍ ሚስጥቹን ከስርቆት የሚጠብቅበት ጥብቅ ህግ ያለው ቢሆንም ይህ ባለሙያ ግን በርካታ ቁልፍ ሰነዶች መሰረቃቸውን ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
የ38 ዓመቱ ዲንግ ከጎግል በየወሩ 14 ሺህ ዶላር ደመወዝ ሲከፍለው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ከወርሃዊ ደመወዝ ባለፈም ቦነስ እና አክስዮን ባለቤት አድርጎት እንደነበርም ተገልጿል፡፡