ጎግል ለሁለት አመት አገልግሎት ያልሰጡ የጂሜል አድራሻዎችን ሊዘጋ ነው
ኩባንያው “ወሳኝ መልዕክቶች፣ መረጃዎች እና ምስሎች የተከማቸበት የጂሜል አድራሻችሁ ከመዘጋቱ በፊት ክፈቱት” ሲል አሳስቧል
ጎግል ከ10 ቀናት በኋላ ነው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አካውንቶችን መዝጋት የሚጀምረው
የአልፋቤት ኩባንያ ንብረት የሆነው ጎግል ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የጂሜል አድራሻዎችን ማጥፋት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ጎግል ከ10 ቀናት በኋላ ነው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የጂሜል አድራሻዎችን መዝጋት እጀምራለሁ ያለው።
የጂሜል አድራሻቸውን ሁለት አመት እና ከዚያ በላይ ያልተጠቀሙበት ሰዎች አድራሻቸውን ከመዘጋት ለመታደግ ከፍተው መልዕክቶችን መለዋወጥ እንደሚገባቸው አሳስቧል።
ጎግል ለረጅም ጊዜ ጥቅም ያልሰጡ የጂሜል አድራሻዎችን እንደሚዘጋ ያስታወቀው በግንቦት ወር ሲሆን በተለያየ ጊዜ የማስታወሻ እና ማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን ሲያደርስ መቆየቱን ገልጿል።
የጂሜል አድራሻዎች መልዕክት ከመለዋወጫነት ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾችን መክፈቻ፣ መረጃ እና ምስሎችን ማከማቻ (ጎግል ዶክስ)፣ ማስታወሻ መያዣ ሆነው እንደማገልገላቸው ከታህሳስ 1 2023 ጀምሮ የሚተገበረው ውሳኔ ሚሊየኖችን ችግር ውስጥ ሊጥል ይችላል ተብሏል።
እናም ውሳኔው የኢሜል አድራሻን ብቻ ሳይሆን በርካታ ወሳኝ መልዕክትና መረጃዎችን ሊያሳጣ ስለሚችል አድራሻዎቹን ከፍቶ መጠቀም እንደሚገባ ነው ጎግል ያሳሰበው።
ከጂሜል አድራሻዎች ጋር የተያያዙ ማህበራዊ ትስስር ገጾችን ለመክፈትም አዳጋች እንደሚሆን ተገልጿል።
ጎግል በሚዘጉት የጂሜል አድራሻዎች ስለተከፈቱ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ንግግር ማድረጉና አስቀድሞ መልዕክት መላኩም ነው የተነገረው።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ደንበኞቹን ከመረጃ ምንተፋ ለመጠበቅ መሆኑን አስታውቋል።
ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የኢሜል አድራሻዎች በመረጃ መንታፊዎች እጅ ለመግባት ቀላል መሆናቸው ይነገራል።