መከላከያ ሚኒስቴር የትግራይ ክልል ስለሰራዊቱ ያወጣውን መግለጫ እንዲያርም ጠየቀ
ክልሉ የሰራዊትም ሆነ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነትና የለውም የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር
ሚኒስቴሩ የክልሉ መግለጫ “የሰራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል…ሃላፊነት የጎደለው” ነው ብሏል
ሚኒስቴሩ የክልሉ መግለጫ “የሰራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል…ሃላፊነት የጎደለው” ነው ብሏል
ከሰሞኑ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ የሰራዊቱን ገለልተኝነት የሚጋፋ እና ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መግለጫ መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ የትግራይ ክልል መንግስት “የሰራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል ሀገራዊና ክልላዊ ተግባሮቹንም በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደናቅፍ ሃላፊነት የጎደለው መግለጫ” ማውጣቱን ገልጿል፡፡
ክልሉ “ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች” በማስተላለፍ ላይ እንደነበረ ያነሳው የመከላከያ ሚኒስቴር “ለህዝቦች ክብር እና ጥቅም ሲባል በከፍተኛ ሃላፊነት መንፈስ ለማለፍ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን” ጠቅሷል፡፡
“የመከላከያ ሰራዊታችን የማንም ፖለቲካ ሀይል፣¸ክልል ወይንም ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብርላቸው¸ሰላምና ደህንነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው የገነቡት ጠንካራ፣ ብሔራዊና ሐገራዊ ተቋም ነው” ሲል ገልጿል ሚኒስቴሩ፡፡
“…የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት እና ተልዕኮ በምንም መልኩ በአንድ አካል ወይም ቡድን ስር የማይወድቅ ህጋዊና ሕገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ ብቻ የሚመራ መሆኑን እያስታወቅን መግለጫውን ያወጣው አካል ስህተቱን በይፋ እንዲያርም” የመከላከያ ሚኒስቴር ጠይቋል፡፡
ማንኛውም አካል የሰራዊቱን ተልዕኮ በሚያደናቅፍ አግባብ መግለጫ ከመስጠት እና አላስፈላጊ መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብም ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ጥሪ ቀርቧል፡፡
የትግራይ ክልል ከሰሞኑ “የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሃይሎች ተወያይተው ከሚያስቀምጧቸው ቀጣይ መፍትሄዎች ውጪ” የመከላከያ ሃይሎችን አደረጃጀትና ስምሪትን የተመለከቱ ወሳኔዎች“ተቀባይነትም ሆነ ተፈፃሚነት የላቸውም” ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይወሳል፡፡
ክልሉ የሰራዊትም ሆነ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብሎም ነበር፡፡
“ይህ መግለጫ ሰራዊቱ ወቅታዊና ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መነሻ አድርጎ ግዳጁን እንዳይፈጽም በሚገድብ አኳኋን የተዛባ ይዘት ያለው መግለጫ ነው” ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
መከላከያ ሰራዊት በህዳሴ ግድብ ላይ ያሉ የደህንነት ስጋቶች ለመመከት ከፍተኛ እየተዘጋጀ ነው፤ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ግድያዎችንና መፈናቀሎችን ለማስቆም መስዋእትነት እየከፈለ ሰላም ለማረጋገጥ የሚሰራን ሰራዊት ስም ማጥፋት ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
መግለጫውን ተከትሎ “አንዳንድ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መከላከያን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ በማስተጋባት ፍጹም የሰራዊቱን ህገ መንግስታዊ ተልዕኮ በማራከስ ተግባር ላይ ተጠምደዋል” ሲል ሚኒስቴሩ አስታቀውቋል፡፡