መከላከያ ሠራዊት ያደራጃቸውን ተጨማሪ ዕዞች “በሴራ የተመላ ስልት” ሲል የትግራይ ክልል መንግሥት ተቃወመ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ የተሰኙ ተጨማሪ ዕዞችን ማደራጀቱ ይታወቃል
የትግራይ ክልል በጀት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቅለትም የክልሉ መንግሥት ጠይቋል
መከላከያ ሠራዊት ያደራጃቸውን ተጨማሪ ዕዞች “በሴራ የተመላ ስልት” ሲል የትግራይ ክልል መንግሥት ተቃወመ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ የተሰኙ ዕዞችን ማደራጀቱን ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ ሠራዊቱ የሚሰጠውን ግዳጅ በፍጥነት ለማከናወን እንዲያስችል በሚል የተደራጁት እንዳሉት ሁለቱም ዕዞች በዚህ ዓመት ወደ ስራ እንደሚገቡም ተገልጿል፡፡
የሁለቱን ዕዞች መደራጀት እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች በተመለከተ መግለጫ ያወጣው እና በፌዴራሉ መንግሥት እውቅና የማይሰጠው የትግራይ ክልል መንግስት የሀገር የዕዞቹን መደራጀት ተቃውሟል፡፡ የክልሉ መንግሥት በመግለጫው እርምጃውን “የሃገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ ለመስጠትና የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ በሴራ የተመላ ስልት” ሲል ገልጾታል፡፡ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በፌስቡክ ገጹ ያሰፈረው መግለጫ እንደሚለው የሠራዊቱ አዲስ አደረጃጀት ዓላማ ፣ ባለፉት 23 ዓመታት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል “እልባት ያላገኘውን” የድንበር ግጭት ለመከላከልና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትግራይ ውስጥ የተሰማሩትን የሀገር መከላከያ ሃይሎች በማዳከም ህዝብንና ሃገርን አሳልፎ ለመስጠት የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡
የክልሉ መንግስት የሥልጣን ጊዜው አብቅቷል በሚል ከመስከረም 25 በኋላ እውቅና አልሰጠውም ያለው የፌዴራሉ መንግሥት “የሀገር መከላከያ ሃይሎችን አደረጃጀትና ስምሪት በተመለከተ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ህጋዊ ሃላፊነትም ሆነ ስልጣን ስለሌለው የተወሰኑት ውሳኔዎች ተቀባይነትም ሆነ ተፈፃሚነት የላቸውም” ብሏል፡፡ “በዚህም መሰረት ከትግራይ ጋር የተያያዙ የስምሪትም ሆነ የአመራርና የአደረጃጀት ለውጦች፣ የሰራዊትም ሆነ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነትና ተፈፃሚነት እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል” ሲልም መግለጫው ያትታል፡፡
የሀገር መከላከያ ሃይሎች “ይህንን ህገወጥና ከህገመንግስታዊ ተልዕኳቸው ውጪ የሚደረግ አደረጃጀትና ስምሪት መቀበል እንደሌለባቸው እናሳስባለን” ይላል ክልሉ ያወጣው መግለጫ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት ስለሚወስደው እርምጃ ያለው ነገር ባይኖርም በዚህ ውሳኔ ምክንያት ለሚፈጠር ችግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጿል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ እና ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ስለ አዲሶቹ እዞች መቋቋም በሰጡት መግለጫ ፣ ዕዞቹ ሠራዊቱ የሚሰጠውን ግዳጅ በፍጥነት ማከናወን እንዲቻል መደራጀታቸውን ገልጸው በውስጥም በውጭም የሚቃጡ ጥቃቶችና ችግሮችን ፈጥነው ለመከላከል እንዲችሉ ታስቦ የተደራጁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ አዲስ የተደራጁት ዕዞች ሲሆኑ የቀደሙት ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብና ምስራቅ ዕዞች ባሉበት እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ያነሳው ሌላው ነጥብ የበጀት ጉዳይ ሲሆን በመግለጫው “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የትግራይ በጀት ሊለቀቅ ይገባል” ብሏል፡፡ ይህ ካልሆነ “በቀጥታ ጦርነት እንደታወጀበት” በመውሰድ በውጤቱ ለሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ “አምባገነን” በሚል የገለጸውን የፌዴራሉን መንግሥት ተጠያቂ እንደሆነ ገልጿል፡፡
“በደህንነትህና ህልውናህ ላይ ያንዣበበው ተጨባጭ አደጋ በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል እንደማይችልና እንደማይገባ ተገንዝበህ እንደወትሮህ ሁሉ ጠላቶችህን ዳግም ለመመከትና ደማቅ ታሪክ ለመስራት ከፍተኛ ዝግጅት እንድታደርግ” ሲልም ለትግራይ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ ወጥ ምርጫ ሥልጣኑን አስቀጥሏል በሚል የፌዴራል መንግስት እና ተቋማቱ ከትግራይ ክልል ህግ አውጪ እና አስፈጻሚ አካላት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ የፌዴራል የበጀት ድጎማም ለነዚህ አካላት በቀጥታ እንዳይሰት ም/ቤቱ ባሳለፈቀው ውሳኔ መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር ለክልሉ መንግሥት በቀድሞው መንገድ የሚያደርገውን የበጀት ፈንድ ከተያዘው የጥቅምት ወር ጀምሮ እንደማይለቅ አስታውቋል፡፡ የበጀት ድጎማውን ለወረዳዎች እና ለከተማ አስተዳደሮች በቀጥታ ለመልቀቅ ዝግጅት ማድረጉንም ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በትግራይ ክልል መንግሥት እና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል የተፈጠሩ ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ከመስከን ይልቅ ይበልጥ እየተባባሱ መሔዳቸውን ቀጥለዋል፡፡