ግለሰቧ በታጠቁ የግል ጠባቂዎቻቸው አስገዳጅነት ነው ከሆስፒታል ያመለጡት
በኮሮና መያዛቸውን ተከትሎ ከሆስፒታል ያመለጡት የኢራቅ የምክር ቤት አባል ጉዳይ እያነጋገረ ነው
በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ አረጋግጠው ሳለ ከሃኪሞች ትዕዛዝ ውጭ ከሆስፒታል ያመለጡት የኢራቅ የምክር ቤት አባል ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡
ማሃሲን ሃምዶን ይባላሉ የተባለላቸው ግለሰቧ በሰሜናዊ ኢራቅ የኒንቬህ ግዛት የምክር ቤት ተወካይ ሲሆኑ በታጠቁ የግል ጠባቂዎቻቸው አስገዳጅነት ነው ምርመራውን ካደረጉበት ሞሱል ሆስፒታል ወጥተው ያመለጡት፡፡
ወደ ሃገሪቱ ዋና ከተማ ባግዳድ የጉዞ ታሪክ የነበራቸው መሆኑን ተከትሎ ባደረጉት ምርመራ ነው በቫይረሱ መያዛቸውን ያረጋገጡት፡፡
በቫይረሱ የተያዙ የመጀመሪያዋ የምክር ቤቱ አባል መሆናቸውንም በግዛቲቱ የሚገኘው የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የግለሰቧን ጠባቂዎች በማውገዝ በህግ እንደሚጠይቁ ያስታወቁ የግዛቲቱ ባለስልጣናት ማሃሲን የሃኪሞቹን ምክረ ሃሳብ አክብረው ወደ ሆስፒታል እንዲመለሱ ስለማሳሰባቸው ዘ ባግዳድ ፖስት ዘግቧል፡፡
በኢራቅ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 24 ሺ 254 መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡