የ2024/25 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ በኦልትራፎርድ ከፉልሃም ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀመራል
የማንቸስተር ዩናይትድ አምበል ፖርቹጋላዊው ብሩኖ ፈርናንዴዝ በክለቡ እስከ 2027 የሚያቆየውን ውል ፈረመ፡፡
በ2020 ዩናይትድን የተቀላቀለው የ29 አመቱ አማካይ በ2022 የተፈራረመው ፊርማ በ2026 የሚጠናቀቅ ሲሆን ለተጨማሪ አንድ አመት በክለቡ ለመቆየት ውሉን አራዝሟል፡፡
ተጫዋቹ ከፊርማ ስነስርአቱ በኋላ ባደረገው ንግግር "ይህን ማልያ መልበስ እና ክለቡን መወከል ምን አይነት ከባድ ሀላፊነት እንደሆነ በደንብ እገነዘባለሁ" ብሏል፡፡
በተጨማሪም ከቡድኑ ጋር ዋንጫዎችን እንደማነሳና ስኬቶችን እንደማይ እርግጠኛ ባልሆን ኖሮ ይህን ውል አላራዝምም ነበር ሲል ተደምጧል።
የማንቸስተር ዩናይትድ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ዳን አሽወርዝ ብሩኖ የቡድኑን ተጫዋቾች እና ሰራተኞች በማስተባበር የተዋጣለት መሪ ነው ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡
ተጫዋቹ በ2020 ከስፖርቲንግ ሊዝበን በ47 ሚሊየን ፓውንድ ዩናይትድን የተቀላቀለ ሲሆን በ2023 ከሃሪ ማጉየር የአምበልነት ስፍራውን በመረከብ ቡድኑን እየመራ ይገኛል፡፡
ብሩኖ ፈረንናዴዝ ለማንቸስተር ዩናይትድ ተሰልፎ ባደረጋቸው 234 ጨዋታዎች 79 ግቦችን ሲያስቆጥር 67 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
በ2023/24 የውድድር ዘመን መጥፎ ጊዜን ያሳለፈው ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቀቅ የኤፍ ኤካፕ ዋንጫ ማንሳት ችሏል፡፡
ቡድኑ በዘንድሮው አመት የተሻለ ሆኖ ለመቅረብ የአማካይ እና የተከላካይ ስፍራ ላይ የሚጫዎቱ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት እያደረገ ቢገኝም አዲሱ የእንግሊዝ ፕርሚየርሊግ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት ተደጋጋሚ ጉዳቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው ወር ዩናይትድ ከአርሰናል ጋር ባደረገውት የአቋም መለኪያ ግጥሚያ በ52 ሚሊየን ፓውንድ የተገዛው አዲሱ ተከላካይ ሌኒ ዮሮ ለሶስት ወራት ከሜዳ የሚርያቀው ጉዳት አጋጥሞታል፡፡
በዚህም አዲሱ የቡድኑ ተከላካይ ዮሮ ዩናይትድ በሊጉ ጅማሮ ከፉልሀም ፣ ከሊቨርፑል ፣ ቶተንሀም እና አስቶንቪላ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ አይሰለፍም፡፡
በተመሳሳይ አጥቂው ራስመስ ሆሉንድ 6 ሳምንታትን ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጥበት ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን ራሽፎርድ እና አንቶኒም በጉዳት ላይ ይገኛሉ፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ በነገው እለት በሜዳው ፉልሀምን በመግጠም የ2024/25 የፕርሚየር ሊግ ጉዞውን ይጀምራል፡፡
ቅዳሜ ደግሞ ሊቨርፑል ፣ አስቶንቪላ ፣ አርሰናል ፣ ኒውካስትል እና ኤቨርተን የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።