ፊፋ ለክለቦች የአለም ዋንጫ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ሽልማት ማዘጋጀቱን አስታወቀ
ተሳታፊ ቡድኖች የጥሎ ማለፍ ውድድሩን መቀላቀል ከጀመሩ በኋላ እንደአፈጻጸማቸው የገንዘብ ተሸላሚ ይሆናሉ

32 የአለም ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር በፈረንጆቹ ሰኔ 14 የሚጀመር ሲሆን አፍሪካ በአራት ክለቦች ትወከላለች
የአለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለክለቦች የአለም ዋንጫ ውድድር ከ1 ቢሊየን ዶላር በላ ሽልማት ማዘጋጀቱን ይፋ አደረገ፡፡
የአውሮፓ ክለቦች ማህበር ማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲን ጨምሮ የአውሮፓ ክለቦችን በመወከል ሲያደርግ የነበረውን ድርድር ተጠናቋል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በውድድሩ የሚሳተፉ ቡድኖች ከሌሎች የአለም አካባቢዎች ከሚመጡ ክለቦች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ከፊፋ ጋር ሲደራደሩ ቆይቷል፡፡
የአውሮፓ ክለቦች ካላቸው ስም እና ዝና እንዲሁም ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት በርካታ ተመልካች ያላቸው የተለያዩ ውድድሮች ሊቋረጡ ስለሚችሉ ይህን ሊያካክስ የሚችል ክፍያ እንዲያገኙ ጠይቋል፡፡
12 የአውሮፓ ክለቦችን ጨምሮ 32 የአለም ክለቦች በ7 ምድቦች ተከፍለው ለትልቁ የገንዘብ ሽልማት የሚፋለሙ ይሆናል፡፡
ፊፋ ባሳለፍነው ታህሳስ አጋማሽ ውድድሩን ለማስተላለፍ ከግዙፉ የስፖርት ፕሮግራሞች ማሰራጫ ዳዛን ጋር በብቸኝነት ውድድሩን እንዲያስተላፍፍ የ1 ቢሊየን ዶላር ስምምነት ፈጽሟል፡፡
በአሜሪካ 12 ስታድየሞች በ11 ከተሞች የሚካሄደው ውድድር የመክፈቻ ግጥሚያውን በፈረንጆቹ ሰኔ 14 አድርጎ ከአንድ ወር በኋላ ሀምሌ 13 በኒው ጀርሲ ፍጻሜውን ያገኛል፡፡
በውድድሩ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያውን የሚቀላቀሉ ሁሉም ቡድኖች የተሳትፎ ክፍያ የሚያገኙ ሲሆን በውድድሩ እንደሚኖራቸው አፈጻጸም እና ቆይታም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙ ይሆናል፡፡
ለአንድ ወር በሚዘልቀው ውድድር የሚገኘው ሁሉም ትርፍ ለተሳታፊ ክለቦች እና ፊፋ በእግር ኳስ ዙሪያ ለሚሰራቸው የልማት ስራዎች እንደሚከፋፈል ማህበሩ አንድም ዶላር ወደካዝናው እንደማያስገባ ተገልጿል፡፡
የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የፊፋ ክለቦች የአለም ዋንጫ የክለቦች እግር ኳስ ቁንጮ ውድድር ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ሰፊ ፉክክር የሚደረግበት እና የአብሮነት ማሳያ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ በግብጹ አል አህሊ፣ በደቡብ አፍሪካው ማማሎዲ ሰንዳውንስ፣ በሞሮኮው ወይዳድ እና በቱኒዚያው ኢኤስ ቱኒዝ በአጠቃላይ በ4 ክለቦች ትወከላለች፡፡