አሜሪካ 240 ሺህ ዩክሬናውያንን ለማባረር ማቀዷ ተነገረ
የትራምፕ አስተዳደር ጦርነትን ሸሽተው አሜሪካ ለገቡ ዩክሬናውያን የተሰጠውን ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለመሰረዝ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል

ከ530 ሺህ በላይ የኩባ፣ ሃይቲ፣ ኒካራጋዋ እና ቬንዙዌላ ስደተኞችም በተመሳሳይ በፍጥነት ከአሜሪካ እንዲወጡ ይደረጋል ተብሏል
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር 240 ሺህ የሚጠጉ ዩክሬናውያንን ከአሜሪካ ለማስወጣት ማቀዱ ተነገረ።
ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን የትራምፕ ባለስልጣን እና ሌሎች ሶስት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው፥ ከአሜሪካ የሚባረሩት ዩክሬናውያን የሩሲያ - ዩክሬን ጦርነትን ሸሽተው አሜሪካ የገቡ ናቸው።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዩክሬናውያኑ በአሜሪካ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ መፍቀዳቸውን ዘገባው አስታውሷል።
የባይደን አስተዳደር ያሳለፈው ውሳኔ ከ1.8 ሚሊየን በላይ ስደተኞች ወደ አሜሪካ በህጋዊ መንገድ እንዲገቡና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ አስችሏል።
በስደተኞች ላይ ጠንካራ አቋም የያዙት ሪፐብሊካኑ ትራምፕ ወደ ስልጣን እንደመጡም ከህገወጥ እና ወንጀለኛ ስደተኞች ባሻገር በባይደን የስልጣን ዘመን በህጋዊ መንገድ እንዲገቡ የተፈቀደላቸውንም ከአሜሪካ ለማባረር እየሰሩ ነው።
ዩክሬናውያኑን ከአሜሪካ የማስወጣቱ ሂደት ትራምፕ እና ዜለንስኪ ባለፈው ሳምንት ካደረጉት ዱላ ቀረሽ የዋይትሃውስ ንትርክ በፊት የተጀመረ መሆኑ ተገልጿል።
የአሜሪካ የሆምላንድ ሴኩሪቲ ቃል አቀባይ ትሪሺያ ማክላፍሊን ግን ተቋማቸው በዩክሬናውያን ስደተኞች ጉዳይ በዚህ ስአት ይፋ የሚያደርገው አዲስ መረጃ እንደሌለው ተናግረዋል።
ዋይትሃውስ እና በአሜሪካ የዩክሬን ኤምባሲም አስተያየት እንዲሰጡ ከሬውተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዳግም ወደነጩ ቤተመንግስት እንደገቡ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች መካከል ስደተኞችን ከአሜሪካ ማስወጣት ላይ ያተኮረው ቀዳሚው ነው። ፕሬዝዳንቱ በግጭት እና ጦርነት ምክንያት የአሜሪካን ድንበር በህጋዊ መንገድ አልፈው ለሚገቡ ሰዎች የሚሰጠውን መብትም ማንሳታቸው ይታወሳል።
በዚህም ከ530 ሺህ በላይ የኩባ፣ ሃይቲ፣ ኒካራጋዋ እና ቬንዙዌላ ስደተኞች እስከዚህ ወር መጨረሻ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃዳቸው ተሰርዞ ወደየመጡበት እንዲመለሱ እየተሰራ መሆኑን የሬውተርስ ምንጮች ተናግረዋል።
አሜሪካ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ ከአፍጋኒስታን ወጥታ ታሊባን ስልጣን ሲቆጣጠር ወደ አሜሪካ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው 70 ሺህ አፍጋናውያንም ከሚባረሩት ውስጥ ናቸው ተብሏል።
ሲቢኤስ ቴሌቪዥን አስቀድሞ ባወጣው ዘገባ በባይደን የስልጣን ዘመን ጊዜያዊም ቢሆን ህጋዊ መብት ያገኙ የነበሩት ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት ዜጎች በፍጥነት ከአሜሪካ እንዲወጡ ከሚደረጉት ስደተኞች መካከል መካተታቸውን ጠቁሟል።