ሃማስ የትራምፕ ተደጋጋሚ ዛቻ ኔታንያሁ በጋዛ ወረራውን እንዲቀጥል ድጋፍ ለመስጠት ያለመ ነው አለ
አዲሱ የእስራኤል ጦር አዛዥ ኢያል ዛሚር በበኩላቸው "ሃማስ ከፍተኛ ኪሳራ ቢደርስበትም ሙሉ በሙሉ አልተሸነፈም፤ ተልዕኳችን ገና ነው" ብለዋል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እስራኤል በጋዛ ግቧን እንድታሳካ "የፈለገችውን እየላክንላት ነው" ማለታቸው ይታወሳል
የፍልስጤሙ ቡድን ሃማስ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት "የመጨረሻ" ነው ተብሎ ለቀረበለት ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጠ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጋዛ የሚገኙት ታጋቾች ሙሉ በሙሉ ካልተለቀቁ "የሃማስ ፍጻሜ ይሆናል፤ የጋዛ ነዋሪዎችም ከፍተኛ ዋጋ ትከፍላላችሁ" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የሃማስ ቃል አቀባይ አብደል ላቲፍ አል ቃኑ ለሬውተርስ በላኩት የጽሁፍ መልዕክት "ታጋቾች የሚለቀቁት እስራኤል በጥር ወር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ዙሪያ ከተስማማች ብቻ ነው" ብለዋል።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የተጠናቀቀውን የመጀመሪያ ምዕራፍ የጋዛ የተኩስ አቁም ለ42 ቀናት ማራዘም እንደምትፈልግ ማስታወቋ ይታወሳል።
ሃማስ በበኩሉ የተኩስ አቁሙን ማራዘም ሳይሆን በአሜሪካና ሌሎች አደራዳሪዎች በጥር ወር በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሁለተኛው ምዕራፍ መጀመር አለበት ባይ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር ከእሁድ ጀምሮ ወደ ጋዛ ማንኛውም የሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ ማድረጉን ተከትሎም ከ2 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ወደ ቀደመው የከፋ ችግር ተመልሰዋል።
ጋዛን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው "የመካከለኛው ምስራቅ ሬቪራ" የማስመሰል እቅዳቸውን ያቀረቡት ትራምፕ በግብጽ የቀረበውን አማራጭ እቅድ ተቃውመው በሃማስና ፍልስጤማውያን ላይ ዛቻ እያሰሙ ነው።
"ይህ ዛቻ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ የሚደረገውን ድርድር ያወሳስበዋል፤ እስራኤል በጋዛ ዳግም ጦርነት እንድትክፈት የሚያበረታታ ነው" ብለዋል የቡድኑ ቃል አቀባይ።
አዲሱ የእስራኤል ጦር አዛዥ ኢያል ዛሚር በትናንትናው እለት የሰጡት አስተያየትም የጋዛው ጦርነት ዳግም የመቀስቀሱ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን ያመላከተ ነው ብሏል ፍራንስ 24 በዘገባው።
አዛዡ ሃማስ ከፍተኛ ኪሳራ ቢደርስበትም ሙሉ በሙሉ እንዳልተሸነፈ በመጥቀስ "ተልዕኳችን ገና ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
በተያያዘ አሜሪካ በሽብርተኝነት ከፈረጀችው ሃማስ ጋር ከፈረንጆቹ 1997 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀጥታ ንግግር ማድረጓ ተገልጿል። የአሜሪካ ታጋቾች ጉዳይ መልዕክተኛው አዳም ቦህለር ከሃማስ አመራሮች ጋር መነጋገራቸውን ዋይትሃውስ አረጋግጧል።
በጋዛ ካሉ ቀሪ 59 ታጋቾች ውስጥ አምስቱ አሜሪካውያን ሲሆኑ አራቱ ህይወታቸው ማለፉን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቅርቡ በተደረገው የእስራኤልና ሃማስ የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ የተለቀቁ ስምንት ታጋቾችን በነጩ ቤተመንግስት ተቀብለው ማነጋገራቸው የሚታወስ ነው።