ሊዮኔል ሜሲ በ2019 የመጀመሪያውን የፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት መውሰዱ ይታወቃል
የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን እና የፓሪስ ሴንት ጀርሜን ተጫዋቹ ሊዮኔል ሜሲ የ2022 የፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብርን ተቀዳጀ።
የ35 አመቱ ኮከብ የፈረንሳይ አጥቂዎቹን ኪሊያን ምባፔ እና ካሪም ቤንዜማ ጋር ተፎካክሮ ነው ሽልማቱን የወሰደው።
በኳታሩ የአለም ዋንጫ ሀገሩን በአምበልነት እየመራ ለክብር ያበቃው ሊዮኔል ሜሲ፥ በ2021/22 የውድድር ዘመን በ49 ጨዋታዎች 27 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ሁለተኛውን የፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት የወሰደው ሜሲ፥ “አስደናቂ አመት ነበር፤ ይህን ሽልማት ማግኘቴም ትልቅ ክብር ነው፤ ይህን ስኬት ያለቡድን አጋሮቼ ድጋፍ ማሳካት አልችልም ነበር” በማለት የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን እና የፒ ኤስ ጂ የቡድን አጋሮቹን አመስግኗል።
“ለረጅም ጊዜ ስመኘው የነበረውን አሳክቼዋለሁ፤ ከዚህ ስኬት ላይ መድረስ የሚችሉት ጥቂቶች ናቸው” ሲልም ተናግሯል።
በምርጥ ግብ ጠባቂ ዘርፍ ደግሞ አርጀንቲናዊው ኢሚሊያኖ ማርቲኔዝ አሸናፊ ሆኗል።
የ30 አመቱ የአስቶንቪላ ግብ ጠባቂ በኳታሩ የአለም ዋንጫ ከፈረንሳይ ጋር የተደረገውን የፍጻሜ ፍልሚያ ጨምሮ አራት የፍጹም ቅጣት ምቶችን በማዳን የአለም ዋንጫው ወደ ቦነስአይረስ እንዲያቀና ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ይታወሳል።
በፓሪስ በተካሄደው የሽልማት ስነስርአት ፥ የአለም ዋንጫው ሻምፒዮን ቡድንን የመሩት ሊዮኔል ስካሎኒ የአመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው ተሸልመዋል።
ስካሎኒ የማንቸስተር ሲቲውን ፔፕ ጋርዲዮላ እና የሪያል ማድሪዱን ካርሎ አንቸሎቴ በመርታት ነው ሽልማቱን የወሰዱት።
የእንግሊዝ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኟ ሳሪና ዊግማን ደግሞ በሴቶቹ ዘርፍ አሸናፊ ሆናለች።
የአመቱን ምርጥ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ሽልማት የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ወስደዋል።