ኢንፋንቲኖ ለሶስተኛ ጊዜ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው የመመረጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው ተባለ
የ52 ዓመቱ ኢንፋንቲኖ በ2016 ሴፕ ብላተርን በመተካት የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው አይዘነጋም
ኢንፋንቲኖ በድጋሚ ከተመረጡ እስከ 2031 ድረስ ፊፋን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ይሆናል
ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ለሶስተኛ ጊዜ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው የመመረጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው ተባለ።
የ52 ዓመቱ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በደፈረንጆቹ በ2016 ሴፕ ብላተርን በመተካት የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።
ስዊዝ-ጣሊያናዊው ኢንፋንቲኖ በፈረንጆቹ በ2019 በድጋሚ ተመርጠው እስከ ቀጣዩ አመት 2023 በፕሬዝዳንትነት በማገልገል ላይ መሆናቸውም ይታወቃል።
የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) ምክር ቤት ሐሙስ እለት ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተውም በሚቀጥለው ዓመት መጋቢት 16 ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኢንፋንቲኖ ያለ ምንም ተቀናቃኝ ብቸኛ እጩ መሆናቸው ነው።
ይህም ኢንፋንቲኖ በዚሁ ከቀጠሉ መጋቢት 16 ቀን 2023 በኪጋሊ በሚካሄደው የፊፋ ጉባኤ ለሶስተኛ ጊዜ የመመረጥ እድላቸው ከፈተኛ መሆኑና ፊፋን እስከ 2031 ድረስ በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ በፊፋ ህግ መሰረት የኢንፋንቲኖ የፕሬዚዳንትነት የመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት - የሴፕ ብላተር የስልጣን ዘመን ተደርገው ስለሚቆጠሩ - ከፕሬዝዳንቱ 12 አመት ገደብ ጋር የማይቆጠሩ ይሆናል።
የፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በየአራት ዓመት እንደሚካሄድ ይታወቃል።
ሴፕ ብላተር እንደፈረንጆቹ በ2015 በሙስና ቅሌት እስከ ታገዱበት ጊዜ ድረስ ለ17 ዓመታት (ከ1998 እስከ 2015) የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው ማገለገላቸው አይዘነጋም።