ፊፋ የአለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር ወደ 64 ለማሳደግ እየመከረ እንደሚገኝ ተነገረ
በማህበሩ ምክር ቤት የቀረበው ሀሳብ አንድ አራተኛ የፊፋ አባል ሀገራት እንዲሳተፉ እድል የሚፈጥር ነው

በ2026ቱ የአለም ዋንጫ የተሳታፊዎች ቁጥር ከ32 ወደ 48 ከፍ ማለቱ ይታወሳል
የአለም እግር ኳስ ማህበር ፊፋ በ2030 የአለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ሀገራትን ቁጥር ወደ 64 ለማሳደግ እያጤነ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
ባሳለፍነው ረብዕ በጀመረው የእግር ኳስ ማህበሩ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ የተነሳው ሀሳብ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ 211 አባል ሀገራት ባሉት ማህበር ወስጥ አንድ አራተኛ ሀገራት እንዲሳተፉ እድል የሚከፍት ነው፡፡
የማህበሩ ቃል አቀባይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ባሳለፍነው ረቡዕ በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ በኡራጋይ አማካኝነት የተሳታፊዎች ቁጥር እንዲያድግ ሀሳብ መቅረቡን እና ማህበሩም ጉዳዩን እያጤነው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ተከታታዮች እና ተወዳጅነት ያለው የአለም ዋንጫ በየአራት አመቱ በተለያዩ ሀገራት አዘጋጅነት ከ1930 ጀምሮ ለ22 ጊዜ ተካሂዷል፡፡
በ18 የተለያዩ ሀገራት አስተናጋጅነት የተካሄደው ውድድር ከጊዜ ወደጊዜ ከተሳትፎ እና ከአካታችነት ኮታ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ስካይ ኒውስ አስነብቧል፡፡
በአሜሪካ ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አዘጋጅነት በሚካሄደው የ2026 የአለም ዋንጫ የተሳታፊዎች ቁጥር ከ32 ቡድኖች ወደ 48 ከፍ እንዲል የእግር ኳስ ማህበሩ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
የ2026 የአለም ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ በርካታ ጨዋታ የሚካሄዱበት ሲሆን በ6 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በ16 አስተናጋጅ ከተሞች 104 ጨዋታዎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሀገራት እግር ኳስ ማህበራት ፊፋ የአለም ዋንጫ ውድድርን ለማስፋት በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ እንዲያማክራቸው ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን አቅርበዋል፡፡
የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የውድድር ተሳታፊዎች ማደግ ተጨማሪ ገቢን እንደሚያስገኝ ፣ በርካታ ብሄራዊ ቡድኖች እንዲሳተፉ እድል እንደሚሰጥ እና እግር ኳስን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ይከራከራሉ፡፡
የአለም እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ቡሊንግሃም በበኩላቸው "በአለም ላይ ያሉ ብዙ ሀገራት በአለም ዋንጫ ፍፃሜዎች የመጫወት እድል እንዳላገኙ አውቃለሁ፤ ይህን ለማድረግ እድሉን እንደሚፈልጉም ግልጽ ነው ነገር ግን ይህንን ከውድድሩ አቅም እና ተወዳጅነት እንዲሁም የማስተናገድ አቅም ጋር ማመጣጠን አለብን” ሲሉ ለስካይ ኒውስ ተናግረዋል፡፡
የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 64 እንዲያድግ በቀረበው ሀሳብ ላይ ፊፋ መች ውሳኔ እንደሚሰጥ ባይታወቅም ሀሳቡ ተቀባይነት ካገኘ ስፔን ፖርቹጋል እና ሞሮኮ በሚያዘጋጁት የ2030ው የአለም ዋንጫ 64 ብሔራዊ ቡድኖችን ልንመለከት እንችላለን፡፡