ኢራን ፕሬዝደንት ትራምፕ ልኬያለሁ ያሉት ደብዳቤ አልደረሰኝም አለች
በተመድ የኢራን ቋሚ ተልእኮ ሀገሪቱ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ምንም አይነት ደብዳቤ አለመቀበሏን በትናንትናው እለት ገልጿል

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የኑክሌር ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉና ለሀገሪቱ አመራር ደብዳቤ መላካቸውን ተናግረዋል
ኢራን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ልኬዋለሁ ያሉት ደብዳቤ አልደረሰኝም አለች።
በተባበሩት መንግስት ድርጅት(ተመድ) የኢራን ቋሚ ተልእኮ ሀገሪቱ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ምንም አይነት ደብዳቤ አለመቀበሏን በትናንትናው እለት ገልጿል።
የኢራን የዲፕሎማሲ ተልእኮ ይህን ያለው ፕሬዚደንት ትራምፕ በኢራን ኑክሌር ፕሮግራም ላይ ንግግር በሚጀመርበት ጉዳይ ለኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ ደብዳቤ መላካቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከኢራን ጋር የኑክሌር ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉና ለሀገሪቱ አመራር ደብዳቤ መላካቸውን ተናግረዋል።ፕሬዝደንቱ አክለውም "ለኢራን የተሻለ ስለሚሆን" ቴህራን ንግግር ለማድረግ ትስማማለች የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል።
"ደብዳቤውን ያገኙታል ብዬ አስባለሁ። ሌላው አማራጭ ሌላ ነገር ማድረግ ነው፤ ምክንያቱም ሌላ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖር አንፈቅድም" ብለዋል ትራምፕ።
በ2015 ኢራን በኑክሌር ፕሮግራሟ ላይ ገደብ እድትጥልና በምትኩ ማዕቀብ እንዲነሳላት ከስድስት የአለም ኃያላን ሀገራት ጋር ስምምነት ፈርማ ነበር። ነገርግን አሜሪካ በ2018 ከስምምነቱ በውጣት ማዕቦቹን መልሳ በመጣሏ ምክንያት ኢራን የተወሰኑ የኑክሌር ፕሮግራሞቿን ድጋሚ እንድትጀምር አስገድዷታል።
ስምምነቱን በድጋሚ ለመጀመር የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ አልሆኑም። የኢራን ባለስልጣናት ኢራን በአሜሪካ ጫና ማዕቀብ ስር ሆና ንግግር ማድረግ አትችልም ሲሉ ይደመጣሉ።