አዲሱ አዋጅ በግጭት ቀጣና ለሚሰሩ የአማራ ክልል ዳኞች ምን ያህል ዋስትና ይሰጣቸዋል?
በክልሉ ሚያዝያ 2015 ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ዳኞች በሰጧቸው ውሳኔዎች ብቻ ለእስርና ግድያ መዳረጋቸውን ክልል አቀፉ የዳኞች ማህበር ገልጿል

ማህበሩ በክልሉ ምክር ቤት የጸደቀው የዳኞች ያለመከሰስ መብት አዋጅ የዳኞችን ስጋት ይቀንሳል ብሏል
በሚያዚያ ወር 2015 የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን መነሻ በማድረግ በአማራ ክልል ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ከአንድ አመት በላይ ለዘለቀ ጊዜ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ እየደረሰ ከሚገኘው ጉዳት ባለፈ የጤና ፣ የትምህርት ፣ የልማት ፣ የትራንስፖርት ፣ የመንግስት ፣ የፍትህ እና ሌሎች ዘርፎች በቀደመው ልክ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡
በሰላም መደፍረሱ ምክንያት በተጽዕኖ ውስጥ እያለፉ ከሚገኙ ዘርፎች መካከል የፍትህ እና የዳኘነት ስርአት አንዱ ነው፡፡
የአማራ ክል ዳኞች ማህበር ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በዳኞች ላይ የሚፈጸመው እስር፣ እንግልት እና ወከባ እየተበራከተ እንደሚገኝ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን አውጥቶ ነበር፡፡
ከ2016 ጀምሮም ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት የሶስት ዳኞች ህይወት ማለፉንም ማህበሩ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህ አካሄድ የዳኝነት ነጻነትን በግልጽ የሚፃረር ከመሆኑም በላይ የሰብዓዊ መብቶች እንዳይከበሩ እና የሕግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ተግባር መሆኑንም ማህበሩ ባወጣቸው መግለጫዎች ኮንኗል፡፡
የማህበሩ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሀኑ አሳሳ ክልሉ ዳኞች ላይ በስራቸው ምክንያት በአስፈጸሚው አካል ጭምር ከፍተኛ እስር ወከባ እና እንግልት የሚደርስበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
“በተለያዩ አካላት እና የመንግስት ሰዎች ዳኞች ከፍተኛ ተጽዕኖ ያስተናግዳሉ፤ ከስራቸው ጋር በተያያዘ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በየጊዜው እንደሚደርሳቸው ለማሕበሩ ሪፖርት የሚያደርጉ ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም” ሲሉ አቶ ብርሀኑ አብራርተዋል፡፡
ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሀኑ አክለውም “ከ2016 አመት ጀምሮ በአጠቃላይ ከ36 በላይ ዳኞች ታስረው ነበር በዚህ አመት ከመስከረም ወር ጀምሮ ደግሞ 13 ዳኞች በእስር ላይ ነበሩ፤ እኛ ባደረግነው ማጣራት መሰረት ዳኞቹ ሌላ የወንጀል ጥፋት ፈጽመው ሳይሆን እስሩ በወሰኗቸው ውሳኔዎች እና ከስራቸው ጋር ብቻ የተያያዘ እንደነበር አረጋግጠናል” ብለዋል፡፡
ባለፈው አመት እና ዘንድሮ ታስረው የነበሩ ሁሉም የክልሉ ዳኞች በአሁኑ ወቅት ከእስር መለቀቃቸውን ማህበሩ ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጧል፡፡
በሌላ በኩል ክልሉ በቅርቡ የዳኞችን ያለመከሰስ መብት እና የፍርድ ቤት ማጠናከሪያ አዋጅ ለክልሉ ምክር ቤት በማቅረብ አጽድቋል፡፡
አዋጁ ከዚህ ቀደም ከአንድ ግዜ በላይ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ ሳይችል የቆየ ቢሆንም በዳኞች ላይ እየበረከተ የመጣውን ተጽዕኖ ምክንያት በማድረግ ማህበሩ እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባደረጉት ግፊት ሊጸድቅ መቻሉን የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል
የማህበሩ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አዋጁን በተመለከተ ባደረጉት ማብራሪያ “የአዋጁ መጽደቅ ዳኞች ከውስጣዊ እና ውጫዊ ተጽዕኖዎች ተላቀው ከጣልቃገብነት ነጻ ሆነው በህግ እና ማሰረጃ ብቻ ተመስርተው ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችላቸው ነው፤ ከዚህ ባለፈ እጅ ከፍንጅ ወይም ከዳኝነት ስራቸው ውጭ ወንጀል ሲሰሩ ካልተገኙ ያለመታሰር መብት እንዲኖራቸው የሚያስችል ስለመሆኑ” አመላክተዋል፡፡
አቶ ብርሀኑ አክለውም “ክልሉ አሁን ከሚገኘበት የሰላም መደፍረስ ሁኔታ አንጻር ህጉ በቶሎ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይደርጋል ተብሎ ባይጠበቅም፤ ቢያንስ ከቀደመው የተሻለ የዳኞችን የስራ ነጻነት ማጎልበት እና ስጋታቸውንም መቀነስ ይችላል ተብሎ እንደሚታሰብ” ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግጭቶች በፍትህ ስርአቱ ላይ የሚያደርሱት ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚገኝ የአማራ ክልል የዳኞች ማህበር ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ያነሳሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው ጠበቃ እና የህግ ባለሙያ ጥጋቡ ደሳለኝ የሰላም መስፈን ፍትህን ወይም ህግን ለማረጋገጥ መሰረታዊ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡
“የህግ ስርአት ከየትኛውም አካል ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ እና አጥፊን ተጠያቂ ለማድረግ የሚዘረጋ ሂደት ነው ፤ የሰላም መደፍረሶች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ስርአቱ ጠንካራ ሆኖ ለመቆም ከመቸገሩ ባለፈ በሂደቱ ላይ የማህበረሰቡ እምነት እንዲቀንስ ፣ ወንጀሎች እንዲበራከቱ እና አገልግሎት ፈላጊውን እንዲሸሽ የሚያደርግ ነው” ብለዋል፡፡
ከዚህ ሀሳብ ጋር የሚስማሙት የአማራ ክልል የዳኞች ማህበር ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሀኑ በበኩላቸው “ይህን በዝርዝር ለማስረዳት ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም እየተመለከትን ከምንገኘው ሁኔታ በመነሳት በዳኞች እና ፍትህ አካላት ላይ ከሚደርሰው እንግልት ባለፈ ማህበረሰቡ ጉዳዮችን ይዞ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚመጣበትን መጠን እንደቀነሰው እየታዘብን ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጦርነትም በህግ ነው የሚመራው የሚሉት ጠበቃ እና የህግ አማካሪው አቶ ጥጋቡ በ1949 በወጣው የጄኒቫ ኮንቬንሽን መሰረት የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከየትኛውም ተፋላሚ ሀይሎች ጥቃት እና እና እንግልት ኢላማ ሊጠበቁ እንደሚገባ መደንገጉን ገልጸዋል፡፡
ግጭት የበላይነት በያዘበት ሁኔታ የፍትህ ስርአት በተገቢው መልኩ ስራውን መስራት አለመቻሉ የብዙ ህገ ወጥነቶች እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ነጸብራቅ ሊሆን ስለሚችል የፍትህ ስርአቱ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግለት አሳስበዋል፡፡
“በሰላም መደፍረስ ወቅት ፍትህ ወይም ህግ የለም የሚሉ አካላት ነገሮችን በሀይል ወደ ማስፈጸሚ ሊገቡ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ደካማዎች ይበልጥ እንዲጎዱ ስርአት አልበኞች ደግሞ የማይገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ሊያደርግ ይችላል፤ ችግሩ በየጊዜው እየታረመ የሚሄድ ካልሆነ ደግሞ ሰላም ከሰፈነ በኋላም ለህግ የበላይነት ዋጋ የማይሰጥ የማህበረሰብ ክፍል እየተበራከተ እንዲሄድ ሊያደርግ ይችላል” ሲሉ የህግ ባለሙያው ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡