በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ውስጥ እየተዋጉ ያሉት የዩክሬን ኃይሎች ከበባ ውስጥ ገብተዋል ተባለ
ከበባው በኩርስክ ግዛት ያላትን ቁጥጥር እንደመደራደሪያ እጠቀምበታለሁ የሚል ተስፋ ሰንቃ ለነበረችው ኪቭ ትልቅ ኪሳራ ነው ተብሏል

የዩክሬን ወታደሮች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የገቡት ዋሽንግተን ለዩክሬን የደህንነት መረጃ ማጋራቷን ካቆመች በኋላ ነው
በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ውስጥ እየተዋጉ ያሉት የዩክሬን ኃይሎች ከበባ ውስጥ ገብተዋል ተባለ።
ባለፈው ክረምት ወቅት በምዕራብ ሩሲያዋ የኩርስ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት የከፈተቱት በሺዎች የሚቆጠሩ የዩክሬን ወታደሮች ከበባ ውስጥ ሊገቡ ጥቂት እንደቀራቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ በኩርስክ ግዛት ያላትን ቁጥጥር ከሩሲያ ጋር በሚደረግ የሰላም ንግግር እንደመደራደሪያ እጠቀምበታለሁ የሚል ተስፋ ሰንቃ ለነበረችው ኪቭ ትልቅ ኪሳራ ነው ተብሏል።
የሩሲያ ኃይሎች በመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የዩክሬን ኃይሎችን ወደ ሁለት ቡድን መክፈላቸውን ተከትሎ በኩርስክ ግዛት ያለው የዩክሬን ሁኔታ ባለፉት ሶስት ቀናት በፍጥነት እየተባባሰ መምጣቱን ዘገባው የግንባር መረጃዎችን የሚተነትነውን ኦፕን ሶርስ ማፕን ጠቅሶ ዘግቧል።
የዩክሬን ወታደሮች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የገቡት ዋሽንግተን ለዩክሬን የደህንነት መረጃ ማጋራቷን ካቆመች በኋላ ሲሆን ወታደሮቹ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ሊቸገሩ ወይም ሊያዙ ይችላሉ ተብሏል።
በግንባር ያለው ሁኔታ የተበላሸው ኪቭ ከሞስሶ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንድታደርግ አሜሪካ እያደረገችባት ያለውን ጫና እጨመረች ባለበት ወቅት ነው።
መቀመጫውን ፊንላድ ያደረገው የብላክ በርድ ግሩፕ ወታደራዊ ተንታኝ ፓሲ ፓሮይኔን "በኩርስክ ግዛት ያለው የዩክሬን ሁኔታ መጥፎ ነው" ብሏል።
"አሁን ላይ የዩክሬን ወታደሮች ሊከበቡ ወይም ተገደው ሊያፈገፍጉ የቀራቸው ጥቂት ነው። በሚያፈገፍጉበት ወቅትም በሩሲያ ከባድ መሳሪያና በድሮን ጉዳት ይደርስባቸዋል" ብሏል ተንታኙ።
በጉዳዩ ላይ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም ሆነ የዩክሬን ጦር ያለው ነገር የለም።
ዩክሬን የሩሲያን ድንበር ጥሳ የገባችው ምስራቅ ዩክሬን የተሰማራው የሩሲያ ኃይል ወደኋላ ያፈገፍጋል በሚል እሳቤ ነበር። ነገርግን ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት በማጠናከር በጦርነቱ የመጀመሪያ ወራት ከነበራት ፍጥነት ጋር በሚመሳሰል መልኩ በርካታ መንደሮችን እየተቆጣጠረች ትገኛለች።