ፊፋ፤ የዴንማርክ ተጫዋቾች “ሰብዓዊ መብት ለሁሉም” የሚል ጽሁፍ ያለው ማሊያ እንዳይለብሱ ከለከለ
የዴንማርክ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሁፉ ይዘት "በውስጡ ምንም አይነት ፖለቲካ የለውም” ብሏል
ፊፋ፤ ተሳታፊ ሀገራት ትኩረታቸው ስፖርት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ በደብዳቤ አሳስቧል
ፊፋ ዴንማርክ ተጫዋቾቿ “ሰብዓዊ መብት ለሁሉም” የሚል ጽሁፍ ያለው የልምምድ ማሊያ እንዲለብሱ ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ፡፡
ፊፋ በኳታር የአለም ዋንጫ ላይ የዴንማርክ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች “ሰብአዊ መብት ለሁሉም” የሚል ጽሁፍ ያለው የልምምድ ማሊያ እንዲለብስ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ፡፡
የዴንማርክ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ጃኮብ ጄንሰን የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) ወሳኔ ቢቀበሉትም ምክንያታዊ እንዳልሆነ ለዴንማርክ የዜና ወኪል ተነግረዋል፡፡
"በውስጡ ምንም አይነት ፖለቲካ አለ ብለን አናስብም። እኛ የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ናቸው ብለን እናስባለን እናም በዚህ አመለካከት እንቆማለን ” ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
"ፊፋ የተለየ ግምገማ አለው እና በሚያሳዝን ሁኔታ ያንን ግምት ውስጥ ማስገባት ነበረብን" ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህ ውሳኔ የመጣው የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና ዋና ጻሀፊ ፋታማ ሳሞራ ወደ ኳታር የሚጓዙ ቡድኖች "በእግር ኳስ ላይ እንዲያተኩሩ" እና ስፖርቱ ወደ እያንዳንዱ የርዕዮተ ዓለም ጦርነት እንዳይጎተት ለሁሉም 32 የዓለም ዋንጫ ቡድኖች ደብዳቤ ከላኩ ከአንድ ሳምንት በኋላ መሆኑ ነው፡፡
ደብዳቤው በኳታር የስደተኛ ሰራተኞች አያያዝ እና የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ በርካታ የዓለም ዋንጫ ቡድኖች ላደረጉት ተቃውሞ ምላሽ ነውም ተብሏል።