ሩሲያ የዩክሬን ጦር መሳሪያዎችን እንዳይታዘዙ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መታጠቋ ተገለጸ
"ስፔትስናዝ" የተሰኘው ቴክኖሎጂ በ10 ኪሎ ሜትር ውስጥ ያሉ መሳሪያዎችን እንዳይታዘዙ ያደርጋል ተብሏል
ሩሲያ ይሄንን የጦር መሳሪያ ከተጠቀመች ኔቶ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተገልጿል
ሩሲያ የዩክሬን ጦር መሳሪያዎችን እንዳይታዘዙ የሚያደርግ ጦር መሳሪያ መታጠቋ ተገለጸ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ዘጠኝ ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ቀርተውታል፡፡
ባለፉት ወራት ውስጥ በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶች የተከሰቱ ሲሆን አሁን ደግሞ በዩክሬን ያለው የሩሲያ ልዩ ጦር ኤሌክትሮ ማግኔቲክስን ተጠቅሞ የዩክሬንን የጦር መሳሪያዎች እንዳይታዘዙ ወይም ከጥቅም ውጪ ሊያድርግ እንደሚችል ተገልጿል።
እንደ ብሪታንያው ታየምስ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ የሩሲያ ልዩ ጦር "ስፔትስናዝ" የተሰኘው ቴክኖሎጂ የታጠቀ ሲሆን ቴክኖሎጂው በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ያሉ የዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን እንዳይታዘዙ ያደርጋል ተብሏል።
ጀስቲን ፕሮንክ በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ተንታኝ ሲሆኑ፤ እሳቸው እንዳሉት ባድ ጋይስ የሚል ስያሜ ያለው የሩሲያ ጦር ቴክኖሎጂ የዩክሬን ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ መሰረተ ልማቶችን ሳይቀር ከጥቅም ውጪ ያደርጋል።
ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ያልሆነ ነገር ግን በመሬት ላይ የሚተኮስ ልዩ ሚሳኤል ያላት ሲሆን ለልዩ ዘመቻ ልትጠቀመው ግን ትችላለችም ተብሏል።
ሩሲያ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ያልሆነ መሳሪያ ማምረቷን ገልጻ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን መምታት እንደሚችልም አስታውቃ ነበር።
ሞስኮ ይሄንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዩክሬንን የጦር መሳሪያዎች እና መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ካደረገች በአካባቢው ያለው የኔቶ ጦርም ኢላማ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል እና ጦርነቱም ሊሰፋ ይችላል ተብሏል።