በፊፋ የሀገራት ደረጃ 9ኛ እና 61ኛ የተቀመጡት ፖርቹጋልና ጋና ዛሬ የምድብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
በ2014ቱ የአለም ዋንጫ ጋና ላይ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ይጠበቃል
በወጣት ተጫዋቾች የተደራጀው የጋና ብሄራዊ ቡድንም ለአፍሪካ ተስፋ ሰጪ ውጤትን እንደሚያሳይ ይገመታል።
የአለም ዋንጬ የምድብ ስምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ጋና እና ፓርቹጋል የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።
ጨዋታው ምሽት 1 ስአት ላይ በመርከብ እቃ መጫኛ ኮንቴነሮች በተሰራው 974 ስታዲየም ይደረጋል።
በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ 9ኛ ላይ የተቀመጠችው ፓርቹጋል የምትጫወተው 61ኛ ደረጃን ከያዘችው አፍሪካዊቷ ጋና ጋር ነው።
በአለም ዋንጫ ተሳትፎም ፓርቹጋል በሶስት ጊዜ ትበልጣለች። ሰባት ጊዜ በአለም ዋንጫው የተሳተፉት ሴሌሳዎቹ ባለፉት 14 የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ያሸነፉት በሶስቱ ብቻ ነው።
በሶስቱ ያለፉት የአለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታዎችም ተሸንፈዋል። ጀርመን ካስተናገደችው የ2006 አለም ዋንጫ ወዲህ ሩብ ፍፃሜ መድረስ አለመቻላቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ።
ቼክ ሪፐብሊካዊው ፌደሪኮ ሳንቶስ የሚያሰለጥኑት ቡድን ግን በኳታር የተሻለ ውጤት ጠብቁ ብለዋል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ መጨረሻው ሊሆን በሚችለው የአለም ዋንጫ የሚያሳየው ብቃትም ይጠበቃል። በ2014ቱ የአለም ዋንጫ ፓርቹጋል ጋናን 2 ለ 1 ስታሸንፍ ጎሎቹን ያስቆጠረው ሮናልዶ መሆኑ የሚታወስ ነው።
የአትሌቲኮ ማድሪዱ ጆኦ ፌሊክስ እና የኤሲ ሚላኑ ራፋኤል ሊዎ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር የፊት መስመሩን ይመራሉ ተብሏል።
የማንቸስተር ከተማ ተቀናቃኝ ክለቦች አማካዮች በርናንዶ ሲልቫ እና ብሩኖ ፌርናንዴዝም የማጥቃቱን ሂደት እንዲያግዙ ነው የሚጠበቀው።
ለአራተኛ ጊዜ በአለም ዋንጫው እየተሳተፈች ያለችው ጋናም በቀላሉ እጅ ትሰጣለች ተብሎ አይጠበቅም።
የክርስቲያል ፓላሱን ጆርዳን አየውና የአርሰናሉን ቶማስ ፓርቴ ያካተተው የኦቶ አዶ ቡድን በወጣቶች የተደራጀ ነው። ጥቋቁሮቹ ከዋክብት በ2010 ለሩብ ፍፃሜ የደረሱቀትን ትልቅ ድል ለማሻሻል የዛሬውን ጨዋታ በድል ሊጀምሩት ይገባል።
በአለም ዋንጫው 17 ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረውን ክርስቲያኖ ሮናልዶ መቆጣጠር ግን እንደሚፈትናቸው ይጠበቃል።
የነልዊስ ፊጎ እና ዴኮ ሀገር ከነአሳሙኣ ጂያን ምድር ምሽት 1 ስአት ትፋለማለች።