“ከስፔን ጋር የምናደርገውን ግጥሚያ እንደ ፍጻሜ ጨዋታ ነው የምንመለከተው”- የጀርመን አሰልጣኝ
በጃፓን 2ለ1 የተሸነፈችው ጀርመን በድጋሚ መሸነፍ እንደማትችል አሰልጣኟ ሀንሲ ፍሊክ አሳውቀዋል
አሰልጣኝ ፍሊክ ከስፔን ጋር የሚኖራቸው ጨዋታ የሞት ሽረት ነው ብለዋል
በኳታር እየተካሄደ ባለው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በዛሬው እለት ከፍተኛ ትኩረት ካገኙ ጨዋታዎች ውስጥ በምድብ 5 ጀርመን ከስፔን የሚያደርጉት ተጠባቂ ነው።
በመጀመሪያዋ ጨዋታ በጃፓን ሁለት ለአንድ የተሸነፈችው ጀርመን በድጋሚ መሸነፍ እንደማትችል አሰልጣኟ ሀንሲ ፍሊክ አሳውቀዋል።
ፍሊክ በቅድመ ጨዋታው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "መልሱ እሁድ ይሰጣል፤ለጥያቄው ሌላ መልስ ይኖረናል፤ ትክክለኛው መልስ" ብለዋል።
በረቡዕ ጨዋታ ጀርመን በካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጀመርያውን አጋማሽ አንድ ለዜሮ እየመራች ቆይታ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩባት ሁለት ጎሎች በጃፓን ተሸንፋለች።
አሰልጣኝ ፍሊክ “የመጨረሻዎቹ ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ጥሩ አልነበሩም” ያሉ ሲሆን፤ "ይህን መድገም አንፈልግም” ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን ከስፔን ጋር ያለን ጨዋታ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን ያሉት አሰልጣኝ ፍሊክ፤ የዛሬው ጨዋታ በዓለም ዋንጫው ለኛ የመጀመሪያው የፍጻሜ ጨዋታ ነው" ከስፔን ጋር የሚኖራቸው ጨዋታ የሞት ሽረት መሆኑን ገልጸዋል።
ፍሎክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ሊሮይ ሳኔ በጨዋታው ይሰለፋል አይሰለፍም የሚለው ቁርጡ አልታወቀም ብለዋል።
በምድብ 5 የመጀመሪያ ጨዋታዋ ላይ ከኮስታሪካ ጋር የተጫወተችው ስፔን ኮስታሪካን 7ለ0 ማሸነፏ ይታወሳል።
በምድብ 5 ጀርመን ከስፔን የሚያደርጉት ተጠባቂ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።