የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔቶን ለመቀላቀል እንቅፋት ሆናለች የተባለችውን ቱርክ ለመጎብኘት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ
ክሪስተርሰን "በአስቸኳይ ወደ አንካራ ለመሄድ መዘጋጀታችንን ለቱርክ መንግስት ቀደም ሲል ምልክት ልኬያለሁ" ብለዋል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስዊድን እና ፊንላንድ ለአንካራ የገቡትን ስላልጠበቁ የኔቶ አባልነት ጥያቄን ለመቀበል እንቸገራለን ማለታቸው ይታወሳል
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ለመቀላቀል ሂደት ላይ ያሉት ስዊድን እና ፊንላንድ በቅርቡ አባል እንደሚሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል እንዲሆኑ አሜሪካ እና ፈረንሳይን ጨምሮ 23 ሀገራት አጽድቀዋል። የቀሩት ሰባት ሀገራትም በቅርቡ እንደሚፈርሙ ይጠበቃል፡፡
ቱርክ ፊንላንድና ስዊድን ቃላቸውን ስላልጠበቁ የኔቶ አባልነት ጥያቄያቸውን እንደማትቀበል ገለጸች
ይሁን እንጅ ሀገራቱ ኔቶን እንዲቀላቀሉ እስካሁን ፊርማቸውን ካላስቀመጡት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነቸው ቱርክ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን አልታወቀም፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሁለቱ የኖርዲክ ሀገራት ለአንካራ የገቡትን ቃል እስኪጠብቁ ድረስ ቱርክ የስዊድን እና የፊንላንድ የኔቶ አባልነት ጥያቄን ትቀበላለች ለማለት እንደማይደፍሩ በቅርቡ መናገራቸው ያታወሳል፡፡
"ለሀገራችን የተገባው ቃል እስኪፈጸም ድረስ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋማችንን እንጠብቃለን" ሲሉም ነበር ኤርዶጋን በአንካራ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር የተደመጡት፡፡
"በስዊድን እና ፊንላንድ የገቡት ቃል መከበሩን አለመፈጸሙን በቅርበት እየተከታተልን ነው፣ በእርግጥ የመጨረሻው ውሳኔ የታላቁ ፓርላማችን ይሆናል" ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
እናም አዲሱ የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ቱርክ ስዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ ህብረትን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ እንድትደግፍ ለማሳሰብ ወደ አንካራ ለማቅናት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የክሪስተርሰን የአንካራ ጉብኝት ዋና ዓላማ የቱርክን ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንን ስዊድን እና ፊንላንድ ለአንካራ የገቡትን ቃል (ሁለቱ ሀገራት የኩርድ ታጣቂዎች መሸሸጊያ እንደማይሆኑ ማረጋገጥ) እንደሚፈጽሙ ለማረጋገጥ እንዲሁም ቱርክ ሁለቱም ሀገራት ወደ ኔቶ ለመቀላቀል በሚያደረጉት ሂደት ድጋፏ እንድትሰጥ ለማድረግ ነው እንደሆነም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ክሪስተርሰን ወደ ስልጣን ከመጡ ከሶስት ቀናት በኋላ ለአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲደርሱ እንደተናገሩት "በአስቸኳይ ወደ አንካራ ለመሄድ መዘጋጀታችንን ለቱርክ መንግስት ቀደም ሲል ምልክት ልኬያለሁ" ብለዋል፡፡
"እንሱ ሲመቻቸውና ሲፍቅዱ ወዲያውኑ አደርገዋለሁ፤ስለዚህ ለዚያ በጣም ተዘጋጅቻለሁ" ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባል ከመሆናቸው በፊት ከሩሲያ ወይም ሌላ ጠላት ጫና የሚደረግባቸው ከሆነ የኔቶ አጋሮች እርምጃ እንደሚወስዱ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ሐሙስ እለት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ስቶልተንበርግ ከስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ስዊድን እና ፊንላንድ በማንኛውም አይነት ጫና ውስጥ ቢገቡ አጋሮች እርምጃ አይወስዱም ብሎ ማሰብ አይቻልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡