የቱርክ ፕሬዝዳንት፤ ፊንላንድ ያለ ስዊድን ኔቶን ልትቀላቀል እንደምትችል ፍንጭ ሰጡ
የኔቶ ወታደራዊ ጥምረት የመሪዎች ስብሰባ በመጪው ሃምሌ ወር በሊትዌኒያ ይካሄዳል
ኤርዶጋን ፤ ስዊድን የእኛን ድጋፍ የምትፍልግ ከሆነ “የኩርድ ታጣቂዎችን” አሳልፋ መስጠጥ አለባት ብለዋል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ፊንላንድ ያለ ስዊድን ኔቶ ልትቀላቀል እንደምትችል ፍንጭ ሰጡ፡፡
የስዊድንን ጥያቄ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ጎን የተወችው አንካራ፤ የፊንላንድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ማጸደቅ እንደምትችልም ጠቁመዋል።
“ቱርክ የፊንላንድን የኔቶ አባልነት እንጂ የስዊድንን አባልነት ማጽደቅ አትችልም” ሲሉም ተናግረዋል ኤርዶጋን እሁድ እለት በተለቀቀው የቪዲዮ ንግግራቸው ላይ፡፡
አስፈላጊ ከሆነ ስለ ፊንላንድ የተለየ ውሳኔ ልናስተላለፍ እንችላለን ያሉት ኤርዶጋን፤ ይህን ስናደርግ “ስዊድን በጣም ትደነግጣለች” ሲሉም ተደምጠዋል።
ኤርዶጋን ስዊድን የእኛን ድጋፍ የምትፍልግ ከሆነ የኩርድ ታጣቂዎችን አሳልፋ መስጠት አለባት ሲሉም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
“የኔቶ አባል ለመሆን ከፈለግሽ እነዚህን አሸባሪዎች ወደ እኛ ትመልሺያለሽ” ሲሉም በድጋሚ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ቱርክ፤ እንደፈረንጆቹ በ2016 የከሸፈውን መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገዋል የምትላቸውን የኩርድ ታጣቂዎችን ትደግፋለች ስትል ስቶክሆልምን ትከሳለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፊንላንድ ለብቻዋ የኔቶ ወታደራዊ ጥምረትን መቀላለቀል እንደምትችል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፔካ ሃቪስቶ አማካኝነት መግለጿ አይዘነጋም፡፡
እናም ይህ በመጪው ሃምሌ ወር በሊትዌኒያ ዋና ከተማ ቪልኒየስ ለሚካሄደው የኔቶ ወታደራዊ ጥምረት የመሪዎች ስብሰባ መልካም ዜና ሊሆን እንሚችል ይገመታል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ ስዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባል ለመሆን ማማልከቻ ማስገባታቸው ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጅ በተለይም ከሌሎች የወታደራዊ ጥምረቱ አባላት በተለየ ሃንጋሪ እና ቱርክ ድጋፍ ካላመስጠታቸው ጋር ተያይዞ ጉዳዩ እየተንከባለለ እዚህ መድረሱ ይታወቃል፡፡