ስዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባል ለመሆን 130 “ሽብርተኞችን” አሳልፈው ሊሰጡኝ ይገባል - ቱርክ
የቱርክ ፓርላማ የሀገራቱን የአባልነት ጥያቄ እንዲያጸድቀው ቅድመ ሁኔታውን ያስቀመጡት ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ናቸው
የስዊድን እና ፊንላንድን የኔቶ የአባልነት ጥያቄ እስካሁን ቱርክ እና ሃንጋሪ አላጸደቁትም
ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶን ለመቀላቀል የጀመሩት ጉዞ እንዲሳካ ቱርክ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች።
የቱርክ ፓርላማ የሀገራቱን የአባልነት ጥያቄ ከማጽደቁ በፊት ሀገራቱ 130 “ሽብርተኞችን” አሳልፈው ሊሰጡን ይገባል ብለዋል ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን።
ሀገራቱ ሽብርተኞችን አሳልፈው ካልሰጡን በፓርላማችን የሀገራቱን የኔቶ አባልነት ጥያቄ አናጸድቀውም ማለታቸውንም ሮይተርስ አስነብቧል።በተለይ ስዊድን ቱርክ በሽብርተኝነት የፈረጀቻቸውን የኩርድ ታጣቂዎች በተመለከተ ግልጽ ያለ አቋም እንድትይዝ ነው ፕሬዝዳንቱ ያሳሰቡት።
የፊንላንድ ፖለቲከኞች ግን የፕሬዝዳንቱን ቅድመ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት በስቶኮልም የኤርዶሃንን ምስል ዘቅዝቀው የያዙ ሰዎች ባካሄዱት መጠነኛ ተቃውሞ ምክንያት የመጣ ነው ብለው ያምናሉ።
በድርጊቱ የተበሳጨችው ቱርክ የስዊድን አምባሳደርን ጠርታ ማብራሪያ መጠየቋ የሚታወስ ነው።በአንካራ ጉብኝት ሊያደርጉ የነበሩትን የስዊድን ፓርላማ አፈ ጉባኤ አንድሬስ ኖርለን ጉዞ መሰረዟም አይዘነጋም።
የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶም የኤርዶሃን አዲስ ቅድመ ሁኔታ በስቶኮልሙ ተቃውሞ መበሳጨታቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ከቱርክ በይፋ የቀረበ “ሽብርተኞችን አሳልፋችሁ ስጡን” ጥያቄ አለመቅረቡንም ያክላሉ።
ሀገራቱ የንግግር እና ስላማዊ ስልፍ መብትን ስለምናከብር የስቶኮልሙን ክስተት ማስቆም አልቻልም ከማለት ውጭ ግን ለኤርዶሃን ቅድመ ሁኔታ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።
ስዊድን እና ፊንላንድ የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት በተቀሰቀሰ ሰሞን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል ለመሆን ግን የ30ዎቹንም አባል ሀገራ ድጋፍ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።ቱርክ እና ሃንጋሪም የሁለቱን ሀገራት የአባልነት ጥያቄ ያላጸደቁ ሀገራት ናቸው።