ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ቱርክ በሰሜናዊ ሶሪያ በሚገኙ የኩርድ ኃይሎች ላይ በርካታ ዘመቻዎችን አድርጋለች
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስቲን ከቱርክ አቻቸው ሁሉሲ አካር ጋር ረቡዕ ዕለት ተነጋግረው አንካራ በሶሪያ አዲስ ዘመቻ ልጀምር ነው ማለቷን በተመለከተ ጠንካራ ተቃውሞ ማንሳታቸው ተነግሯል።
ሚንስትሩ ቱርክ በሶሪያ ወታደራዊ ዘመቻ እንዳትጀምር ማሳሰባቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ፔንታጎንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ቱርክ በሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ ከፊል ራስ ገዝ በሆኑ የኩርድ ግዛቶች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸም የጀመረችው ከኢስታንቡል የቦምብ ጥቃት ጀርባ የኩርድ ታጣቂዎች ናቸው ማለቷን ተከትሎ ነበር።
አንካራ ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድም በሶሪያ በምድር ጦር የታገዘ ጥቃት እንደምትጀምር ማስታወቋ ይታወሳል።
የፔንታጎን መግለጫ “ሚንስትር ኦስቲን ጦር ሰበቃው እንዲቀንስ ጥሪ አቅርቧል። እናም መከላከያ ሚንስቴር በሶሪያ ለሚካሄደው አዲስ የቱርክ ወታደራዊ ዘመቻ ጠንካራ ተቃውሞ አጋርቷል።" ብሏል።
በኢስታንቡል ጥቃት ለተገደሉ ሰዎችም ማዘናቸውንም ገልጸዋል ነው የተባለው።
የኦስቲን ጥሪ የመጣው የፔንታጎን የፕሬስ ጸሐፊ ቱርክ በምድር ወደ ሶሪያ መግባቱ በኢራቅ እና እስላማዊ መንግሥት ላይ የተገኘውን ድሎችን “በጣም አደጋ ላይ ይጥላል” ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው ። በዚህ የአሜሪካ ግኝት የሶሪያ ኩርድ ኃይሎች ማዕከላዊ ሚና ነበራቸው ተብሏል።
ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ቱርክ በሰሜናዊ ሶሪያ በሚገኙ የኩርድ ኃይሎች ላይ በርካታ ዘመቻዎችን አድርጋለች። ይህም በድንበር አካባቢ ያሉ ቦታዎችን እንድትቆጣጠር አስችሏታል።