ወጪያቸው ከበደኝ ያለችው ፊንላንድ ከቻይና በውሰት የወሰደቻቸውን ሁለት ፓንዳዎች መለሰች
ፊንላንድ ፓንዳዎቹን ለ15 ዓመታት በውሰት ለማቆየት በሚል ነበር ከቻይና የወሰደቻቸው
ሀገሪቱ ለፓንዳዎቹ በዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ በማድረግ ላይ ነበረች
ወጪያቸው ከበደኝ ያለችው ፊንላንድ ከቻይና በውሰት የወሰደቻቸውን ሁለት ፓንዳዎች መለሰች።
አውሮፓዊቷ ፊንላንድ በፈረንጆቹ 2018 ላይ ነበር ከቻይና ሁለት ፓንዳዎችን የተዋሰችው።
ፓንዳዎቹ በፊንላንድ ለ15 ዓመታት እንዲቆዩ ስምምነት የነበረ ቢሆንም ሀገሪቱ ከስምምነቱ በፊት ፓንዳዎቹን ለመመለስ ወስናለች።
ጎብኚዎችን ለመሳብ በሚል እንስሳቱን ከቻይና የተዋሰችው ፊንላንድ የፓንዳዎቹን ውጪ አልቻልኩትም ብላለች።
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ ከሆነ ፊንላንድ ለሁለቱ ፓንዳዎች በዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ እያወጣች መሆኗን አስታውቃለች።
ከወጪ መብዛት ባለፈም ፊንላንድ ያሰበችውን ያህል ጎብኚዎችን ወደ ሀገሯ መሳብ አለመቻሏ ፓንዳዎቹን ለቻይና እንድትመልስ ሌላኛውም ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል።
ፊንላንድ በቅርቡ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶን በአባልነት የተቀላቀለች ሲሆን ለዩክሬን ድጋፍ እያደረጉ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ሀገሪቱ በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ምክንያት የዋጋ ንረት ካጋጠማቹው ሀገራት መካከልም ፊንላንድ ዋነኛዋ ስትሆን የመንግስት ወጪ መብዛት ፓንዳዎቹ እንዲመለሱ አድርጓልም ተብሏል።
የፊንላንድ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ ፓንዳዎቹ ወደ ቻይና እንዲመለሱ የተወሰነው ከቻይና ጋር ባለ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምክንያት አይደለም ብሏል።