ተሽከርካሪው ጉዞዎችን ከመንገራገጭ ነጻ በሆነ መንገድ ማድረግ እንደሚያስችል ተገልጿል
የፊንላንዱ ኩባንያ ባለ18 ጎማ ተሽከርካሪ ሰራ።
ምስራቅ አውሮፓዋ ፊንላንድ ያለ አንድ ፋብሪካ 18 ጎማዎች ያሉት አዲስ የሞተር ተሽከርካሪ መስራቱን አስታውቋል።
18ዊልስኢንክ የተሰኘው ይህ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ በተለይም ያለምንም መንገራገጭ መንዳት እና መጓዝ ለሚፈልጉ ሰዎች ተመራጭ ነው ተብሏል።
ኩባንያው ለምን ይህን ለየት ያለ ሞተር ሳይክል ተሽከርካሪ እንደሰራው ሲጠየቅ ከመሬት ጋር ተስማሚ የሆነ ተሽከርካሪን ለደንበኞች ለማቅረብ በማሰብ እንደሆነ አስታውቋል።
እንዲሁም ወጣ ገባ የመሬት ገጽታ ባላቸው መንገዶች ላይ ጉዞን በፍጥነት እና እንከን አልባ እንዲሆን በማሰብ ሞተር ሳይክሉ እንደተሰራ ተገልጿል።
18 ጎማዎች የተገጠሙለት ይህ ሞተር ሳይክል በአይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለ ሲሆን ኩባንያው ስለ ምርቱ ምንነት ይፋ ካደረገ በኋላ በአውሮፓ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
አዲሱ ሞተር ሳይክል ስራው ከአንድ ዓመት በፊት ተጠናቋል የተባለ ሲሆን ምርቱ ለህዝብ የተዋወቀው ግን አሁን እንደሆነ ተገልጿል።
ከቀጣዩ ጥቅምት ወር ጀምሮም አዲሱ ተሽከርካሪ ለሸማቾች ዝግጁ ይሆናል ተብሏል።
ሞተር ሳይክሉ በተገጠሙለት 18 ጎማዎች ምክንያት በመንገድ ላይ ያሉ ነገሮች እንደ ዛፍ እና ገዘፍ ያሉ አለቶችን በቀላሉ ያለምንም መንገራገጭ ማለፍ እንደሚችልም ተገልጿል።