3 ሺህ ተሽከርካሪዎችን ጭና በመጓዝ ላይ የነበረች መርከብ ተቃጠለች
መርከቧ ከጀርመን ወደ ግብጽ በመጓዝ ላይ እያለች ሆላንድ አምስተርዳም ላይ አደጋው ደርሶባታል
በእሳት አደጋው የአንድ ሰው ህይወት አልፏል ተብሏል
ሶስት ሺህ ተሽከርካሪዎችን ጭና በመጓዝ ላይ የነበረች መርከብ መቃጠሏ ተነገረ።
መነሻዋን ጀርመን መዳረሻዋን ደግሞ ግብጽ ያደረገችው እቃ ጫኝ መርከብ በሆላንድ አምስተርዳም መቃጠሏን ሮይተርስ ዘግቧል።
ንብረትነቷ የፓናማ የሆነችው ይህች መርከብ በደረሰባት አደጋ የጫነቻቸው ሶስት ሺህ ተሽከርካሪዎች በሙሉ ተቃጥለዋል ተብሏል።
የሆላንድ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በመርከቧ ላይ የደረሰውን አደጋ ለመቆጣጠር ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ተገልጿል።
የመርከቧን ሰራተኞች ለማትረፍ በተደረገው ርብርብ አብዛኞቹን ማትረፍ ቢቻልም አንድ ሰው ግን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቶ ህይወቱ ማለፉን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የሆላንድ ውሀ ትራንስፖርት ድርጅት እንዳለው በእሳት ከተያያዘችው መርከብ ላይ 23 ሰራተኞችን በሂሊኮፕተር ተንጠላጥለው እንዲወጡ ማድረግ ተችሏል።
በመርከቧ ላይ እየነደደ ያለውን እሳት ለማጥፋት ተጨማሪ ውሀ መጠቀም መርከቧን ሊያሰምጣት ይችላል በሚል ተትቷል ነው የተባለው።
ለመርከቧ በእሳት መያያዝ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን ይፋ ያልተደረገ ሲሆን እሳቱ አሁንም አለመጥፋቱ ተገልጿል።
መርከቧ ከጫነቻቸው 3 ሺክ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 350 የጀርመኑ ማርቸዲስ ቤንዝ ስሪት የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ነበሩም ተብሏል።
ተሽከርካሪዎቹን ትረከብ የነበረችው ግብጽ ስለወደመው ንብረት እስካሁን ያለችው ነገር የለም።
በአውሮፓ ያጋጠመው ከፍተኛ የሙቀት መጠን በመርከቧ ላይ ለደረሰው እሳት አደጋ መነሻ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።